“የፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል ከሀገር ሀብቶችና ቅርሶች መካከል አንዱ ነው”፦ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Spread the love

የፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል ከሀገር ሀብቶችና ቅርሶች መካከል አንዱ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

አገልግሎቱ የፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

እንኳን ለፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ተመዝግቦ የሚገኘው የፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል ከሀገር ሀብቶችና ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

በዓሉ ዘንድሮ በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ መጋቢት 18 በሲዳማ ባህል አዳራሽ እንዲሁም መጋቢት 19/2017 ዓ.ም በሶሬሳ ጉዱማሌ በተለያዩ ትዕይንቶች ታጅቦ በድምቀት ይከበራል።

ፊቼ ጫምባላላ በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ የአዲስ ዘመን መለወጫና ማብሰሪያ ሆኖ የሚከበር ታላቅ በዓል ነው። ይህ በዓል በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ባህላዊ ትውፊት ነው።

ፊቼ ጫምባላላ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመረዳዳት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበትም ነው። በዓሉ የሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለወጫ በዓል ብቻም ሳይሆን የነበረ ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ይቅርታ የሚሰፍንበት የእርቅና የሰላም ባህላዊ ትውፊት ነው። በመሆኑም ፊቼ ጫምባላላ የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ ተምሳሌት የሆነ ቅርሳችን ነው።

የሲዳማ ሕዝብ የራሱ የሆነ የቀን አቆጣጠር ያለው ሲሆን ቀናትን፣ ሳምንታንና ወራትን በራሱ ባህላዊ የአቆጣጠር ዘዴ ተከትሎ ይጠቀማል። በበዓሉ ከሰው እስከ እንስሳት እንዲሁም ለዕፅዋትና አራዊቶች መልካም ምኞት የሚንጸባረቅበት ትውፊት ነው። በመሆኑም በዓሉ የቀደምት አባቶችን የዕውቀት ከፍታ ማሳያ፣ የሕዝቡን የጥበብ ጥግ ታሪክ ባለቤትነት መገለጫም ጭምር ነው።

በዓሉ የሲዳማን ሕዝብ ማንነትና ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈም የክልሉን የቱሪዝም ልማትና ዕድገት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም ፊቼ ጫምባላላ የእርቅ፣ የሰላም፣ የአብሮነት እና የወንድማማችነት እሴቶች ከማጎልበቱም ባሻገር ለሀገር ግንባታና የወል ትርክትን ለመገንባት የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው።

ስለሆነም መልካም ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

እንኳን ለፊቼ ጫምባላላ አደረሳችሁ! የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *