
በሀገራችን ብሎም በክልላችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ነዋሪዎች ማድረስና ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን እዉን ለማድረግ እየተሰራ እንዳለ እሙን ነዉ፡፡
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች ለማድረስና ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን እዉን ለማድረግ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በዚህም ተቋሙ ካቀዳቸው ግቦች መነሻነት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ታከለ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል ፡፡መልካም ንባብ!
የመ/ኮ– እንተዋወቅ ስዎትን ቢገልጹልኝ
አቶ ታከለ ታደሰ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ ነኝ
የመ/ኮ– የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም ለህዝባችን ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ መሠረታዊ የጤና አግልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለዉ ይታወቃልና በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ስላለዉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ጅምር ተግባራትን እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ታከለ ታደሰ ፡- የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በክልሉ የተጀመረው በ2009ዓ.ም አምስት (5) ወረዳዎችን በመያዝ በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከሱሪ ወረዳ በስተቀር በክልሉ ውስጥ ባሉት 41 የገጠር ወረዳዎች እና 19 ከተማ አስተዳደሮች በድምሩ በ60 መዋቅሮች ውስጥ ያሉ አባወራ/እማወራዎች በ48 የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተቋም ታቅፈው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
የመ/ኮ-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሽፋኑን ለማሳደግ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ክልላዊ የንቅናቄ ዘመቻ ተደርጎ ነበር በተደረገው እንቅስቃሴ ምን ውጤት ተገኘ?
አቶ ታከለ ታደሰ ፡-ክልላዊ ንቅናቄ ጥር 30/2017ዓ.ም በቦንጋ ከተማ ሲካሄድ የነባር አባላት ዕድሳት ምጣኔ 8%፤አዲስ አባል ማፍራት ምጣኔ 0.4% እና አጠቃላይ አባልነት ምጣኔ 3.6% ሲሆን ይህ ዝቅተኛ አፈጻጸም መሆኑ በጥልቀት ከተገመገመ በኋላ በየካቲት ወር በተደረገ ዘመቻ ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች፤ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ሚዛን አማን ቅ/ጽ/ቤት በቅንጅት ባደረጉት ትግልና ርብርብ እስከ መጋቢት 07/2017 ዓ.ም ያለው አፈጻጸም ነባር አባላት እድሳት ምጣኔ እንደክልል 85.47%፤አዲስ አባል ማፍራት ምጣኔ 40.62% እና አጠቃላይ አባልነት ምጣኔ 60.2% ልደርስ ችሏል፡፡የነባር አባላት ዕድሳት ሀገራዊ እና ክልላዊ ግብ 95% እና ከዚያ በላይ እንዲሁም አዲስ አባል ማፍራት ምጣኔ ግብ 85% እና ከዚያ በላይ ስለሆነ እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀሪ ቀናቶች በመረባረብ ግቡን ማሳካት ይጠበቃል!!!!
የመ/ኮ-በተያዘው በጀት ዓመት ዜጎችን በተሟላ መልኩ የማህበረሰበ አቀፍ ጤና መድህን መርሀ-ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ አዲስ አባል ማፍራትና ነባር አባላት እድሳት ላይ እየተሰራ እንዳለ ይታወቃልና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተደራሽ የሚሆነዉ ለማን ለማን ነዉ?
አቶ ታከለ ታደሰ ፡-መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ የተሰማሩና በገጠር የሚኖሩ አርሶ አደሮች፤አርብቶ አደሮች እና በከተማ የሚኖሩና በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጀተው የሚሰሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡መደበኛ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች በዚህ ማዕቀፍ የማይካተቱ ሲሆን በቀጣይ ማህበራዊ ጤና መድህን ሲጀመር ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የመ/ኮ፡-የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት እያላቸዉ በአቅም ዉስንነት ምክንያት መክፈል የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል?
አቶ ታከለ ታደሰ ፡-ከፍሎ አባል መሆን የማይችሉና ምንም ገቢ የሌላቸው የህበረተሰብ ክፍሎች በቀበሌ ደረጃ ተለይተውና በሚመለከታቸው ኮሚቴ አባላት ፍጹም ደሃ መሆናቸው ተረጋግጦ በቀበሌ ማህተምና መሸኛ ዝርዝራቸው ወደ ወረዳ ከተላከ በኋላ በወረዳው ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ቦርድ ውይይት ተደርጎበት መክፈል የማይችሉ ተብሎ ከጸደቀ በኋላ ለአንድ መክፈል የማይችል አባወራ/እማወራ 720 ብር አመታዊ መዋጮ የሚከፈል ስለሆነ 30% ድርሻ ወረዳ/ከተማ አስ/ር ፤30% ዞን እና 40% የበጀት ድርሻ የክልሉ መንግስት ሸፍኖ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎቱን ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የመ/ኮ-የማህበሰብ አቀፍ ጤና መድህን መርሀ-ግብር የጤና አግልግሎት ፍትሀዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያለመ ሰው ተኮር ፕሮግራም መሆኑ እሙን ነዉ፤ በዚህም አቅመ ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ የበጎ ተግባራትን የሚያከናዉኑ ወገኖች አሉ? ካሉስ ምንምን በጎ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ?
አቶ ታከለ ታደሰ ፡-በክልሉ ውስጥ ያሉ ኢንቨስተሮች፤የክሊኒክ ባለቤቶች የተለያዬ ፕሮጀክት ባለቤቶች እና ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ አካላቶች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አመታዊ መዋጮ ለመክፈል አቅም ላጡት የህበረተሰብ ክፍሎች እንደ ገቢ መጠናቸው ገንዘብ በማዋጣት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል፡፡
የመ/ኮ-በአጠቃላይ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አሁናዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ጠቅለል አድርገዉ ብገልጹልን
አቶ ታከለ ታደሰ ፡-አስከ የካቲት 30/2017 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 399,400 አባላትን ማፍራት የተቻለ ሲሆን የዕቅዱን 60.2% ማሳካት ተችሏል፡፡
ከገንዘብ አሰባሰብ አንጻር ከከፋይ አባላት ብር 340,459,821 ማሰባሰብ ተችሏል ። የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የዕድሳትና አዲስ አባላት ምዝገባ ስራም እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ/ም ተጠናክሮ የሚቀጥልም ይሆናል ።
የመ/ኮ-ከእኛ ጋር ላደረጉት ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን
አቶ ታከለ ታደሰ -እኔም አመሰግናለሁ!
በካሳሁን አሰፋ
