በክልሉ የሞዴል አርሶአደሮች የመስክ በዓል ተከበረ።

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በክልሉ ግብርና ቢሮና በደቡብ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል አዘጋጅነት በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ ገሊት ቀበሌ የሞዴል አርሶአደሮች የመስክ ቀን ተከብሮ ውሏል።

በበዓሉም በዞኑ ደቡብ ቤንች ወረዳ ጌሊት ቀበሌ በሞዴል አርሶአደሮች የለማው የበልግ የበቆሎ ምርት በክልል ከፍተኛ አመራሮችና በፕሮግራሙ ከሚደግፉ ወረዳዎች በተገኙበት ባለሙያዎች የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

በጉብኝቱ በ “አልካብ” ክላስተር በ38 ሄክታር ላይ በኩታ ገጠም እርሻ የለማው የበቆሎ ማሳ ተጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በክልሉ 11 ወረዳዎች የግብርና ግብዓት በማቅረብ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ በበቆሎና በሰሊጥ ሰብሎች የኩታ ገጠም እርሻ ስራዎችን በማለማመድ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የሊሙ በቆሎ ዘር በ1 መቶ 72 ሄክታር በአርሶአደር ማሳ ማልማቱ ተነግሯል።

ለምርትና ምርታማነትን ዕድገት ተግዳሮት ሆኖ የቆየውን የግብር ትራንስፎርሜሽን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ለግብርና ስራዎች የተሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ የክልሉ መንግሥት ከግብርና ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በኢንስቲትዩት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በክልሉ እየተስተዋለ ያለውን የዘር አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የጎላ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተግባራት ከመደበኛው የእርሻ ስራ የተሻለና ውጤታማ በመሆኑ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው አቶ ማስረሻ ያሳሰቡት።

በአርሶ አደር በዓሉ የተገኙት በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ክላስተር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳኛቸው ልዑሌ የኩታ ገጠም እርሻ በተቀናጀ የባለሙያ ድጋፍና በተሟላ ግብዓት የሚታገዝ በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።

ዶ/ር ዳኛቸው አክለው ግብርናን ለማሻገር በሚደረገው ጥረት ባለሙያዎችና አመራሮች ቅንጅቱን አጠናከረው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በጉብኝቱ በአርሶአደሮች በ1500 ሄክታር እያለማ የሚገኘው የቀይ ሽንኩርት ማሳ ተጎብኝቷል።

በዞኑ በበልግ ከ84ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር የተሸፈነ ከዚህም ውስጥ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቦቆሎ ማሳ መሸፈኑን ከዞኑ ግብርና፣ህብረት ስራና ደን መምሪያ የተገኘዉ መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *