የማጃንግ ብሔረሰብ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየምለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል። ኮሚቴዉ

Spread the love

የማጃንግ ብሔረሰብን የቀደሙ የባህል እሴቶችና ቋንቋ ለማነቃቃት እና ለልማት ለማዋል ያለመ ታላቅ የባህልና የቋንቋ ሲምፖዚየም የካቲት 4 እና 5 በቴፒ ከተማ እንደሚካሄድ የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሐንስ በንዲ ገለጹ።

አቶ ዮሐንስ እንደገለጹት፣ ለሲምፖዚየሙ የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በሙሉ ተጠናቀዋል።

የሲምፖዚየሙ ዋና ዓላማ ለረዥም ጊዜ ተዘንግተው የነበሩ የማጃንግ ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶችንና የአኗኗር ዘይቤዎችን እንደገና ማንቃት መሆኑን ጠቁመዋል።

የብሔረሰቡን አዎንታዊ የባህል እሴቶችን ከመደበኛው ሕግ ጋር በማጣጣም ለሰላም ግንባታና ለግጭት አፈታት መጠቀም፣ በብሔረሰቡ ታሪክ፣ ቋንቋና ልማት ዙሪያ ጠንካራ የማኅበራዊ ትስስርና የሥራ ባህል መፍጠር እንዲሁም ቋንቋና ባህሉን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሲምፖዚየሙ ዋና ትኩረቶች መሆናቸው አመላክተዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ ከጋምቤላና ከደቡብ ምዕራብ ክልል የሚገኙ የማጃንግ ብሔረሰብ ተወላጆችና ወዳጆች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዲሁም የሌሎች ብሔረሰቦች ተወካዮች እና የተጋበዙ እንግዶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል ።

በዕለቱ የብሔረሰቡን ማንነት የሚገልጹ የባህል ትርኢቶች፣ የባህልና የምግብ ትርኢቶች፣የቁሳቁስና የምግብ አውደ ርዕይ እንዲሁም የማጃንግ ቋንቋና ባህልን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪ እንደ አዲስ መወለድ የሚቆጠረውና የራሱ የሆነ አከባበር ያለው የማጃንግ የዘመን መለወጫ በዓል በዚሁ መድረክ ላይ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል ።

አቶ ዮሐንስ አክለውም ቴፒ ከተማ የበርካታ ብሔርና ብሔረሰቦች መገኛ በመሆኗ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ተብላ መጠራቷን በማስታወስ፣ በዞኑና በጎረቤት ዞኖች የሚኖሩ ሁሉም ሕዝቦች በዚህ ታሪካዊ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም ላይ ተገኝተው የማጃንግ ብሔረሰብን እሴቶች እንዲጋሩ ጥሪ አቅርበዋል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *