





በኢትዮጵያ የስንዴ ልማትን “በመስኖ ላይ የተመሰረተ የስንዴ ምርት ከውጭ ከመቀበል ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት ሥራ ውጤታማ እየኾነ እንደሚገኝ ከግብርና ሚኒስትር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በክልላችን ተጨባጭ፣ በክልሉ ምሥረታ ወቅት የመስኖ አውታር ከነበረበት አነስተኛ ሽፋን አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ትርጉም ባለው መልኩ መሻሻል አሳይቷል።
ምንም እንኳን ስንዴ በተፈጥሮው ቀዝቃዛ አየር የሚመርጥ ቢኾንም ሞቃታማ በሆኑ የክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ጭምር የመስኖ ውሃን በመጠቀም ስንዴን በስፋት ማምረት ተችሏል።
በዳውሮ ዞን፣ ማረቃ ወረዳ፣ ጌንዶ ባቾ ቀበሌ በክልሉ መንግሥት በዘላቂ የልማት ግቦች የተገነባውን የውኒ አነስተኛ መስኖ ተጠቅሞ በኩታ ገጠም የበጋ ስንዴ የሚያለሙ አርሶአደሮች የመስኖ አውታር መገንባት አዲስ ተስፋን የሰነቀ እንደኾነ ተናግረዋል።
አርሶአደር አስረስ ዘለቀ እና ግርማ ከበደ ÷
ከዚህ በፊት ስንዴ በአከባቢው ተመርተው እንደማይታወቅ በመግለጽ አሁን ላይ የመስኖ ውሃ ተጠቅሞ በኩታ ገጠም የዘሩት የስንዴ በተሻለ ይዞታ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይ የጓሮ አትክልት በማምረት ለአከባቢው ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመኾን ዕቅድ እንዳላቸው የገለፁት አርሶአደሮቹ÷ የመንግሥት ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
“የውኒ ወንዝ ሰው ከመብላት፣ ሰው ወደ ማብላት ተሸጋግሯል” ያሉት አርሶአደሮቹ÷ መንግሥት የዘረጋውን የመስኖ መሠረተ ልማት በተገቢው በመጠበቅ ቀጣይነት ያለውን ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የቀበሌው የግብርና ባለሙያ አቶ ተሻለ ተክሌ በበኩላቸው÷ መስኖን ተጠቅሞ 10 አርሶአደሮች በአምስት ሄክታር የበጋ ስንዴ እያለሙ እንደኾነ በመግለጽ አርሶአደሮችን ውጤታማ ለማድረግ ተከታታይነት ያለቅ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ ነው ተብለዋል
በአከባቢው በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት፣ አመቱን ሙሉ የሚፈሰው የውኒ ወንዝ እንዲሁም ሊሰራ የሚችል የሰው ኃይል ቢኖርም የመስኖ መሠረተ ልማት ያልተዘረጋ በመኾኑ ምርታማ መኾን እንዳልተቻለ የሚገለጸው ባለሙያው፣
አሁን ላይ በክልሉ መንግሥት የበጀት ድጋፍ የተገነባው አነስተኛ መስኖ ይህንን ችግር የሚቀርፍ በመኾኑ አርሶ አደሩን በኩታ-ገጠም በማደራጀትና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ እንዲኾኑ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለመስኖ ስንዴ ልማት መንግስት የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ፤የተሻሻሉ የመስኖ ስንዴ ሰብል አመራረት ቴክኖሎጂዎችንና አሠራሮችን በማካተት የስንዴ ምርታማነትንና ጥራትን በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሰራል ብሏል ባለሙያው።
በዕድገቱ በዛብህ
