ስራ ፈጣሪ ዜጋን ለማፍራት ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ኮሌጅ ያለው ሚና የጎላ መሆኑ ተገለፀ

Spread the love

የቃራዎ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 89 ሰልጣኞች በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡

በዳውሮ ዞን ከሚገኙ አምስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት መካከል የቃራዎ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አንዱ ሲሆን ኮሌጁ በ2013 ዓ.ም ወደ ስራ መግባቱን ኮሌጁ ዲን አዲሱ ዘካሪያስ ገልፀዋል።

በዚህም በሰባት ትምህርት ዘርፎች በርካታ ሰልጣኞች እያሰለጠነ ሲሆን በዛሬው ዕለት በአይስቲና (ICT) እና በኮንስትራክሽን ሙያ ዘርፍ በመደበኛና በማታ ያሰለጠናቸውን 89 ሰልጣኞችን በደረጃ አራት ለመጀመሪያ ጊዜ አስመርቋል።

ተመራቂ ሰልጣኞች በሰለጠኑት ሙያ መስክ ስራ ጠባቂዎች ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪዎች በመሆን በቁርጠኝነት፣ በትጋት እና በታማኝነት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ዲኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሌጁ አሁን በሰባት ሙያ መስኮች በመደበኛ 211 እና በአጫጭር ስልጠና 249 ሰልጣኞችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ ዲኑ ተናግረዋል።

የዕለቱ ክብር እንግዳና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያዊ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቴክንክና ሙያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስፋው በበኩላቸው ሀገራችን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በምታደርገው ሽግግር ኮሌጁ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑና ለአከባቢው መልካም ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል።

ይህም መንግስት ለስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የስራ፣ ክህሎት የኢንተርፕራይዝና ኢንዲስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ይርጉ፤ የቃራዎ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ከመንግሥት የተሰጠውን ሀላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተው ይህ ትጋት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የዛባ ጋዞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ባፌ በተላ በበኩላቸው በሀገር ደረጃ የተጀመረውን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ብቁና ስራ ፈጣሪ ዜጋን በመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ኮሌጁ ለዛባ ጋዞ ወረዳ እና ለአጎራባች ወረዳ ለሚገኙ ህብረተሰብ ክፍሎች በአቅራቢያው ተጠቃሚ እንድሆኑ ማስቻሉን አቶ ባፌ ጠቁመዋል።

ተመራቂ ሰልጣኞች፤ አሰልጣኞች ስልጠናው ተግባር ተኮር በመሆኑ ቀጣይ በለተያዩ ስራ ዘርፎች ለመሰማራት የሚያግዝ እንደሆነም ገልፀዋል።

ኮሌጁ በዕለቱ 35 ወንድና 54 ሴት ሠልጣኞችን በደረጃ አራት አስመርቀዋል ሲል ደሬቴድ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *