
ሙስናን በመከላከል በክልሉ ከ216 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል፦ የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን
ሙስናና ብልሹ አሰራር ልማትን በማዳከም የሀገር ኢኮኖሚ እንዲገታ፣ የሞራልና የሥነምግባር ቀውስ እንዲባባስ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ ህዝብ በመንግስትና በህግ የበላይነት ላይ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደረግ አደገኛና ድንበር ዘለል ባህሪ ያለው አለማቀፋዊ ወንጀል ነው፡፡
ለዚህምመንግሥት ሙስና የሚያስከትለውን ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በመረዳት ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ለመከላከል እና ለመዋጋት እንዲረዳ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን በማቋቋምኮሚሽኑም የተሰጡትን ተግባር እና ኃላፊነቶች እንዲወጣ አስፈላጊውን የአደረጃጀት በማጠናከር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር መንግስት ቁርጠኝነትና ድጋፍ ያለው መሆኑን አሳይቷል፡፡
ሙስና በክልላችን የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን በማደናቀፍ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዳከም ህዝቡን እያመራረ የሚገኝ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስነ-ምግበርና ፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ገልፀዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት እና የህዝብ ሀብት እንዳይመዘበር በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሙስናን የመከላከል ስራ ተልዕኮ አንግቦ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
ለዚህም የክልሉ ስነ ምግባር እና ፀረሙስና ኮሚሽን የመከላከል ትግሉ ህዝባዊ መሠረት ያለው እንዲሆን ባለድርሻ አካላትን በተገቢው እያሳተፈ የመከላከሉን ተግባር በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የህግ ማዕቀፍ የሚፈልጉ ህጎችን በአዲስ መልክ የማውጣት ስራ የተሰረበት መሆኑን ነው ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ የገለጹት ፡፡
የክልሉ መንግሥት የክልሉ ስነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 17/2015 ማውጣቱ ለዚህ ዋናኛ መረጋገጫ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አዋጅ በዋናነት የስነ ምግባርና ሞራል ግድፈቶችን በብቃት ለመገንባት፣ የሙስና ወንጀልና ብልሹ አሰራርን መከላከል እና ለፀረ ሙስና ትግል አጋዥ የሆነ ህዝብ በመፍጠር የትግሉ ባለቤት እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ክልላዊ የፀረሙስና ቀንን በማክበር ለአዲስ ስነ ምግባር መከታታያ መኮንኖች የአሰልጣኝ ስልጠ እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት ጭምር ስልጠና በመስጠት የክልሉ ስነምግባር እና ፀረሙስና ትግሉ ቀዳሚ አጋር የማድረግ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል ፡፡
ኮሚሽኑ ስራውን የጀመረው በ12 ባለሙያዎች ሲሆን በየዓመቱ የሰው ሃይሉን እየጨመረ በአሁኑ ሰዓት ወደ 24 በማድረስ የአገልግሎት አሰጣጡን በተደራጀና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ እየከወነ መሆኑ፡፡
በአስተዳደር ጽ/ቤት ስር የተደራጁ የስነምግባር መከታታያ መኮንኖች በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርተው ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ቀድመው ላይተው በላቀ ሁላንታናዊ ዝግጅት የመከላከል ስራዎች በመጀመራቸው የሙስና መከላከል ስራ በጋራ ርብርብ እየተሰራ መልካም ውጤቶችን አስገኝቷል፡፡
ኮሚሽኑ ክልላዊ የሙስና መከላከል ተልዕኮ በቀዳሚነት የማስተባበር ሚና ለመወጣት የተቋማዊ የሪፎርም ጉዳዮች፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ እና ህዝባዊ ትስስር የማጠንከር ስራን በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኮሚሽኑ ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት በሙሉ ግልጽ እና አስተማሪ በሆነ ሁኔታ እየሄዱ መሆኑን ለማረጋገጥ የመልካም አስተዳደር ዕቅድ በማቀድ በሚፈጠሩ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የመፍትሔ እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የስነ ምግባር ሞራል ግንባታ ለማሳደግ ኮሚሽኑ ሙስናንና ብልሹ አሰራሮችን በብቃት መግታት እንዲቻል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር 212 ሺህ 38 የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ መስጠቱን ተናግረዋል።
የሙስና ተገላጭነት ስጋት፣ ጥናትና ምርምርን ለማሳደግ በአንድ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች የሙስና መከላከል የአሠራር ስርዓት መዘርጋቱን ገልፀዋል፡፡
በነባሩ ደቡብ ክልል በተጠኑ 36 የአሠራር ስርዓት ጥናቶች እንዳሉ የጠቀሱት ኮሚሽነሩ በእነዚህን የአሠራር ስርዓት ጥናቶች ላይ 4 ዙር የትግበራ ስርዓት ክትትልና ግምገማ የማድረግ ስራ ተሰርቷልም ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከህብረተሰቡ 1 ሺህ 1 መቶ 16 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ቀርበው በሚገባ ተተንትነው ከነዚህም ውስጥ 4 መቶ 37 ጥቆማዎች የሙስና ወንጀል ስለመፈፀሙ የሚጠቁሙ በመሆናቸው ለፖሊስ እና ለፍትህ የተላከ መሆኑን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ሀብትና ንብረት ለመመዝበርና ለመጭበርበር በሀሳብ ደረጀ የተጠነሰሱ እና በአሠራር ደረጃ የተዘጋጁ የሙስና ወንጀሎችን ክልካላ እንዲደረግ ከህብረተሰቡ የቀረቡ 6 መቶ 13 ጥቆማዎችን አስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ ተሰርቶ በአስተዳደራዊ መንገድ መፍታት መቻሉን ገልጸዋል ።
በአስቸኳይ የሙስና መከላከል አገልግሎት ክትትል በማድረግ ብር 128 ሚሊየን 878 ሺህ 3 መቶ 81 ብር ከ51ሣንቲም ማስመለስ የተቻለ ሲሆን በአይነት 1ሺህ 9 መቶ 85 ሄክታር የገጠር መሬት፣ 287 ሺህ 8 መቶ 80 ነጥብ 21 ካሬ የከተማ መሬት፣ 2መቶ 83 ጥራዝ ካሪን፣ 42 ዴስክ ቶፕ ኮምፕዩቴር፣ 2መቶ 92 ካሬ የወላል ምንጣፍ፣ 1 የመንግሥት ቤት፣ 16 ላፕቶፕ፣ 2 የመኪና መለዋወጫ ዕቃ፣ 10 ኩንታል ምርጥ ዘር፣ 2 ታብሌት ሞባይል እንዲሁም ሌሎች የዋጋ ተመን ያልወጠላቸው ንብረቶችን እንዲመለሱ መደረጉን ኮሚሽነር ሙሉሰው ጠቁመዋል፡፡
ባክኖ የነበረ የመንግሥት ሀብት ከማስመለስ አኳያ በገንዘብ 87 ሚሊየን 693 ሺህ 6 መቶ3 ብር ከ31 ሣንቲም የተመለሰ ሲሆን በአይነት 22ሺህ 21 ነጥብ 82 ካሬ የከተማ መሬት፣ 28ሺህ 1መቶ 75 ሄክታር የገጠር መሬት፣ 46 ጥራዝ ካሪን፣ 4የጦር መሣሪያ፣ 12 ታብሌት ሞባይል፣ 4ሞደል 22 ካሪንዎች፣ 1 መቶ 26 ኩንታል አፈር ማዳበሪያ እና 1 ሞተር ሳይክል ማስመለስ የተቻለ መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት፡፡
በአጠቃላይ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ በአስቸኳይ ሙስና መከላከል እና ባክኖ የነበረ 216 ሚሊየን 571ሺህ 984 ብር 82 ሣንትም ማዳን ተችሏል፡፡
ከሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘም በመንግሥት ተቋማት እና በልማት ድርጅቶች የተመደቡ 4ሺህ 405 አመራሮችና ባለሙያዎች እራሳቸውን ላልተገባ ጥቅም እና ሙስና እንዳይደረጉ ሀብታቸውን ማስመዝገባቸውንና አስመዝጋቢዎች ያስመዘገቡት ሀብት ትክክለኛነት የማጣራት ስራ ተሰርቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ይህ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አንስተዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመከላከልና በመቆጣጠር እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ከኮሚሽኑ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ሙስና በረቀቀ ስልት የሚፈፀም ወንጀል መሆኑንጠቁመው፤ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የክልሉ ህዝብ ሙስና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት ተገንዝቦ ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የፀረ- ሙስና ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
