





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የድጋፍና ክትትል ግብረ-መልስ መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት የትምህርት ጥራት በማሻሻል በሁሉም ደረጃ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወኑን ነው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የቢሮው ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በመክፈቻ ንግግራቸው የጠቆሙት።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ከመሠረቱ ለማሻሻል በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተግባራዊ የኾነው የሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ኢንሼቲቭ አዎንታዊ ወጤት እያስገኘ እንደሚገኝ ነው አቶ አልማው የገለጹት።
የ60 ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በኅብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አልማው፥ ከነዚህም ውስጥ የ26ቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ወደ ማስተማር ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ የትምህርት ጥራትን ከማሻሻል በተጨማሪ የትምህርት ተሳትፎ ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደጉን የገለጹት አቶ አልማው በዚህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስነጻጸር 60ሺህ አዳዲስ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ95ሺህ በላይ ተማሪዎች በማኅበረሰብ ራስ አገዝ የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መኾናቸውን የጠቆሙት አቶ አልማው በቀጣይ በተሟላ መልኩ በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ከ371 ሚሊዮን ብር በላይ ከማኅበረሰብ በማሰባሰብ ጅምር የትምህርት ቤት የደረጃ ማሻሻያና የትምህርት ቤት ቁሳቁስ የማሟላት ተግባር እየተከናወነ መኾኑን የገለጹት ኃላፊው፥ ተግባሩን በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በበጀት ዓመቱ በትምህርት ተሳትፎ፣ በጥራትና የፈተና ዝግጅት የተጀማመሩ ተግባራትን ቀጣይነት ባለው መልኩ ውጤታማ እንዲኾን የትምህርት አመራር ቁርጠኝነት መጠናከር አለበት ብለዋል አቶ አልማው።
“ትምህርት የዘላቂ ትውልድ ግንባታ ነው” ያሉት የአቶ አልማው፥ አጠቃላይ የትምህርት ልማት ተግባር አፈጻጸም በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ተቀራራቢ እንዲኾን መድረኩ የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነት ለሁሉም የትምህርት አመራር የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በመድረኩ የድጋፍና ክትትል ሪፖርት አፈጻጸም እየቀረበ የሚገኝ ሲኾን ከክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
