ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥና የዳበረ ዴሞክራሲን ለማስፈን የመንግስታትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይሰራል

Spread the love

ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥና የዳበረ ዴሞክራሲን ለማስፈን የመንግስታትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይሰራል

ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥና የዳበረ ዴሞክራሲን ለማስፈን የመንግስታት ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የህብር ቀንን ምክንያት በማድረግ ” ሰላማችንን ማጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት ” በሚል መሪ ሐሳብ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የፓናል ውይይት አካሂዷል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የዳበረ ዴሞክራሲና ሀገራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግስታት ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል።

የመንግስታት ግንኙነት በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት በፖሊሲና አፈጻጸም ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ግንኙነትና መስተጋብር የሚመለከት ነው።

የህግ አውጪው፣ የህግ አስፈጻሚውና የዳኝነት አካላት እንዲሁም የፌዴራል መንግስት፣ የክልል መንግስታትና የአካባቢ አስተዳደር አካላት በፖሊሲ አፈጻጸም ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ግንኙነትና መስተጋብር የመንግስታት ግንኙነትን እንደሚመለከት አብራርተዋል።

የመንግስታት ግንኙነት የፌዴራል ስርዓት ደም ስር ነው ያሉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የደም ስሩ ጤናማ ሲሆን ህያውና ጠንካራ እንደሚሆን አብራርተዋል።

ህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት የመንግስታት ግንኙነት በሀገራዊ፣ ክልላዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች መካከል ሚዛን የሚያስጠብቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ትብብርንና ቅንጅትን በማጎልበት በህዝቦች መካከል አብሮነትንና መተማመንን ለማጎልበት እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የመንግስታት ግንኙነትን ውጤታማ ማድረግ የተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎችን ለማሳካት እንደሚያስችልም አስታውቀዋል፡፡

የመንግስታት ግንኙነት የአመራር አካላትን አስተሳሰብ በመቅረጽና ገዥ ትርክቶች የበላይነት እንዲኖራቸው በማድረግ ሀገራዊ የጋራ መርሆዎችና ዓላማዎችን ለማስረጽ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ይህም አስተሳሳሪ የሆነ ገዠ ትርክት በማስረጽ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመፍጠር አገራዊ ግንባታን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመንግስታት ግንኙነትን ማጠናከር የጋራ ብልጽግና ለማረጋገጥ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

የመንግስታት ግንኙነት መጠናከር በፌዴራል መንግስትና በክልሎች መካከል መደጋገፍን ለመፍጠር፣ የልማት ልዩነቶችን ለማጥበብና ተመጣጣኝ እድገት ለማምጣት ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የመንግስታት ግንኙነት መጠናከር ግጭትን በመከላከል፣ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለመንግስታት ግንኙነት ውጤታማነት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያነሱት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም፥ ፓርቲው የህብረ ብሄራዊ አንድነት ትርክትን በውጤታማነት ለመተግበር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

የመንግስታት ግንኙነትን የሚወስነው አዋጅ መውጣቱ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሰላም ሚኒስቴር እንዲከታተሉ እና እንዲያስተባብሩ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው መሆኑ ሌላው ምቹ ሁኔታ ነው ብለዋል።

ለዚህ ውጤታማነት የአመራሩ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የመንግስታት ግንኙነት መድረኮችን ማጠናከር እንዲሁም የፓርቲ መሪነት ሚናን በብቃትና በዲስፕሊን መወጣት በቀጣይ በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የመንግስታት ግንኙነት ዘላቂ ሰላምን፣ የዳበረ ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲን ለመገንባት እና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ዋስትና በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ይከታተላሉን 👇

📌በፌስቡክ https://www.facebook.com/sowestcommunication/

📌በድረገጽ www.southwestcomunications.gov.et

📌በኢንስታግራም https://instagram.com/southwest_communications

📌በትዊተር twitter.com/sweprs

📌በቲክቶክ https://www.tiktok.com/@southwest.communi

📌በቴሌግራም https://t.me/Debubmierab

📌በዩቲዩብ youtube.com/@southwestgovcommunication

📌በዋትስአፕ

https://whatsapp.com/channel/0029VbAiSCpGE56ue7VyJJ3x

📌በሊንክደን

https://www.linkedin.com/company/southwest-communications

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *