




የካፌቾ ብሔር የዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በዓል፣ ከባህላዊ ክዋኔው ባሻገር ለዘመናት የዘለቀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስርዓትንም የያዘ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ።
አቶ ማስረሻ ይህን የተናገሩ የብሔሩ ተወላጆች የፌደራል ተቋማት ኃላፊዎች፣ የዩኔስኮ ተወካዮች፣ አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የማሽቃሮ በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ነው።
“የካፋ ህዝብ መለያ የሆነውና ለዓለም ያበረከተው ጥቅጥቅ ደን፣ የማሽቃሮ በዓል ቀጥተኛ ትሩፋት ነው” ያሉት አቶ ማስረሻ፣ “የባህል መሪዎች (ምክሬቾ) በማሽቃሮ ዋዜማ ሲሰባሰቡ ቀድመው የሚገመግሙት የ’ሻሮ’ (የደን) ሁኔታን ነው። ይህ የሚያሳየው በዓሉ ከተፈጥሮ ጋር ምን ያህል የተቆራኘ እንደሆነ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስትም ማሽቃሮን በዩኔስኮ የማስመዝገብ ሂደት እውን እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኃላፊው አረጋግጠዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፣ “የዘንድሮው በዓል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድል በተበሰረበትና የንጉሡ ቅርሶች ወደ መንበራቸው በተመለሱበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መከበሩ ልዩና የድርብ ደስታ ምንጭ ያደርገዋል” ብለዋል።
ማሽቃሮ በ1897 መከበር ካቆመ በኋላ፣ በ1998 በድጋሚ መከበር ከጀመረ ወዲህ እሴቶቹን ሙሉ በማድረግ ለትውልድ ለማሻገር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ ይህ የፓናል ውይይትም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የውይይት መድረኩ በቅርቡ ላረፉት የባህል አምባሳደር እጩ ዶ/ር ሻተራሻ ወርቁ ዓለሙ እና ለአምባሳደር ዘውዴ ኦቶሮ የህሊና ጸሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን፣ በንጉስ ኮላ ዎቾች በተመራው የባህል ምክር ቤትና በሽማግሌዎች ምርቃት በይፋ ተከፍቷል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
