ኢንስቲትዩቱ 123 ቴክኖሎጂዎችን በማሸጋገር ለተጠቃሚ አርሶና አርብቶ አደሮች ማድረስ ተችሏል።

Spread the love

የደቡብ ሞዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዓመታዊ የምርሞር ኮንፈረንስ ግምገማ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መሠረቶች አንዱ የግብርና ክፍሌ ኢኮኖሚ መሆኑን የገለጹት የክልሉ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ ኢንስቲትዩቱ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ያለው አበረታች ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የክልሉን የግብርና እምቅ አቅም በተገቢው በመለየት በተቀናጀ መልኩ በምርምር በማስደገፍ ምርታማነቱን ማሳደግ ከኢንስቲትዩቱ የሚጠበቅ መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ነጋ በዚህም የክልሉ የምግብ ሉዓላዊነት በተሟላ መልኩ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የክልሉን አርሶና ከፊል አርብቶአደር የግብርና ግብዓት ፍላጎት በማሟላት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባው በመግለጽ የክልሉ መንግሥት የአርሶአደሩን ህይወት በዘላቂነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሻሻል የሚከናወኑ የምርምር እና የስርፀት ስራዎች በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ዓለሙ በበኩላቸው፥ በተቋሙ እስካሁን 218 ቴክኖሎጂዎችን እና መረጃዎችን በሰብል፣ በተፈጥሮ ሀብት እና በእንስሳት እርባታ ማላመድና ማፍለቅ የተቻለ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ 123 ቴክኖሎጂዎችን በማሸጋገር ለተጠቃሚ አርሶና አርብቶ አደሮች ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የክልሉን የግብርና ልማት ፖሊሲ መሠረት ያደረገ በዋነኛነት የግብርና ቴክኖሎጂ የማላመድ፤ የማፍለቅ፣ የመፈተሽ፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራር ዘዴዎችን ውጤታማነታቸውን በአርሶ/ አርብቶ አደሩ ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም፤ ውጤታማነታቸው የተረጋገጠላቸውን መነሻ ቴክኖሎጂ የማባዛት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የገለጹት።

ኢንስትቲዩቱ በስሩ ባሉት የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በ4ቱ ዞኖች፣ በታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል በ2 ዞኖች ተደራሽ በመሆን በግብርና ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እየፈታ እንደሚገኝ ያብራሩት አቶ አማኑኤል በዚህም የምርታማነት፣ የአየር ንብረት ለዉጥ፣ የአርሶ/አርብቶ አደር የዘር ፍላጎት ማሟልትን፣ የዝሪያ ማሻሻያ፣ የአፈር አሲዳማነት፣ የተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ ማዳበሪያ አመጣጠንና አጠቃቀም ላይ በሰፊዉ አቅዶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የመነሻ ዘር ብዜትን በተመለከተ የተሻሻለ የቦንጋ በግ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ባቄላ፣ አተር፣ ገብስ፣ቡና፣ ቨርም ወርም፣ ስኳር ዲንች፣ የወጥ ደንች፣ ሙዝ እና የመኖ መነሻ ዘር በማባዛት ለአባዥ አካላትና ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ መቻሉንም እንዲሁ።

በምርምር ኮንፈረንሱ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ (ዶ/ር) የባለድርሻ አካላት ቅንጅት በማጠናከር የአርሶአደሩን ህይወት የሚያሻሽል የግብርና ምርምር ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ክልሉ ከ8 መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአሲዳ የተጠቃ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተመስገን ይህም በክልሉ ለግብርና ሥራዎች ምርታማነት ችግር መሠረታዊ ማነቆ በመሆኑ በተገቢው በማከምና በምርምር የዳበሩ የግብርና ዝርያዎችና ቴክናሎጂን በመጠቀም ምርታማነት ማሳደግ ይገባል ብሏል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *