የሀገር ሀብት የሆነ ቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ስራ በህግና በስርዓት ሊመራ ይገባል ። አቶ ማስረሻ በላቸው ።

Spread the love

በክልሉ ግብርና ቢሮ ቡና፣ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከብሔራዊ የቡና ማህበር ጋር በመተባበር በቡና ጥራት አጠባበቅና ግብይት ዙሪያ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አድርጓል ።

በመድረኩ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የቡና ልማትና ግብይት መጠናከር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከማገዙም ባሻገር ወደ ዲጅታል ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን ተኪ የሌለው ሚና አለዉ ብለዋል።

በክልሉ ከ560 ሺህ በላይ ሄክታር የቡና ማሳ መኖሩን የተናገሩት አቶ ማስረሻ በላቸው ይህም በአርሶአደሩ እና በአልሚ ባለሀብቶች እየለማ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

በዘርፉ የተሰማሩ ቡና የሀገር ሀብትና ኢኮኖሚ በመሆኑ ይህንን የጋራ ሀብት ጥራትን በማስጠበቅና ህገወጥ ግብይትን በመከላከል የሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር የሚገልጽበትን ቡና በህግና በስርዓት መምራት ይገባልም ብለዋል።

በዕለቱ በነበረው የምክክር መድረክ የቡና፣ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ክልላዊ የቡና ጥራት፣ቁጥጥርና ህገወጥ ግብይትን የተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል።

የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ሰብሎች ልማት ለክልላችን አልሚ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች ፤ በንግዱ ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎችና አጠቃላይ ማህበረሰብ የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑንም አቶ አስራት ተናግረዋል ፡፡

የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እና የኑሮ ደረጃ በመወሰን ያለው ሚና የጎላ ሲሆን በሀገር ደረጃም ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው የኤክስፖርት ምርቶች የቡና ምርት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚያስገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የተመሠረተዉን ብሔራዊ የቡና ማህበር ተከትሎ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቡና አቅራቢዎችና አዘጋጆች ዘርፍ ማህበር ምሥረታ ተከናውናል።

የማህበሩ መመስረት በቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አንጻር በንግዱና በመንግሥት መካከል እንደድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ነው ሲሉም ተናግረዋል ።

በዕለቱ ተሳታፊ የሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ በቡና ጥራት ቁጥጥርና ህገወጥ ንግድን ከመከላከል ባሻገር ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ የማህበር ምስረታውን እንደሚደግፉ ተናግረዋል ።

የማህበሩ መመስረት ለንግዱ ህብረተሰብ ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጠት፣የአባላትን መብት እና ጥቅም ማስጠበቅ፣የሀገሪቷ ምርቶች እና አገልግሎቶች እንዲታወቁ እና ገበያ እንዲያገኙ ማድረግ ዓላማ እንዳለው የብሔራዊ ቡና ማህበር ሰብሳቢ አቶ ፈጠነ የኋላሸት ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቡና አቅራቢዎችና አዘጋጆች ዘርፍ ማህበር ስድስት አባላት ስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴዎች የተመረጡ ሲሆን አቶ ዝናቡ አባመጫ የማህበሩ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።


በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *