




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን “ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ቃል ከዞን፣ ከወረዳና ከተማ አስተዳደር ለተወጣጡ ፖሊስ አመራሮችና አባላት ያዘጋጀውን ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ነው።
በስልጠናው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ዋና አፈጉባኤ ክቡር አቶ ወንድሙ ኩርታ: ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዓለም፣ ከአፈሪካ እንዲሁም ከቀጣናዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ተቃኝተው የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልጸው ሠልጣኞች ሀገራችን የያዘችውን ቀና አቋም ለማፅናት እንዲያውሉ አውስተዋል።
ሀገራችን ከለውጡ ማግስት እንደ ቀድሞ እልህ አስጨራሽ የፖሊስ ትግል የታየበት ውጤት አስመዝግባለች ያሉት ዋና አፈጉባኤው: የክልላችን ፖሊስም ለክልሉ ምስረታ እውን መሆን የተጫወቱት አወንታዊ ሚና ላቅ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ ፖሊስ መዋቅር በርካታ ሪፎርም እንደተደረገበት ያወሱት ክቡር ወንድሙ ኩርታ: ተተኪ አባላትን ለማፍራት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ከማድረጉም በሻገር ምክር ቤቱ የተለመደውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በሀገራችን ላይ እየተመዘገቡ ባሉ እምርታዊ ለውጦች የአብዛኛዎቹ አይን እየቀላ ነው ያሉት ክቡር አቶ ወንድሙ ኩርታ: ከዝህ የተሻለ ለውጥ ለማምጣትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የላቀ ቁርጠኝነትና የዓላማ ፅናትን ያነገበ የፖሊስ አባላት ሊኖር ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ: ስልጠናው የዓለም ሁኔታ በተወሳሰበበት ሰዓት የሚሰጥ መሆኑ ልዩ ያደርጋል ብለው የሀገሪቱን ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመናና ፍላጎት የተረዳ የፖሊስ አመራርና አባላት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በዲጂታሉ ዓለም ውስብስብ ወንጀሎች የሚፈጠሩበት ጊዜም ጭምር ስለሆነ ይህኑኑ ተረድተውና ተንትነው የሚያስተዳደር የፀጥታ መዋቅር ለሀገራችን አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ሀብታሙ አክለው ገልፀዋል።
የክልላችን ፖሊስ አባላትና አመራር ለብሔራዊ ጥቅም የሚቆም እንዲሆን ይሰራል ያሉት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሳ: ይህንኑ የሚያጠናክር ስልጠና ስለሆነ በትኩረት ተከታትለው ለታችኞቹ አባላት እንዲያደርሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ስልጠናውን በአጭር ማብራሪያ የጀመሩት የፌደራል ፖሊስ የህግና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ፋሲል አሻግሬ: ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና በሚል ርዕስ የሚሰጠው ስልጠና ሀገር አቀፍ የፖሊሲ ሰነድ በመሆኑ ልዩ አፅንኦት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
ረዳት ኮሚሽነሩ አክለው ጂኦስትራቴጂያዊ አውድን ለሀገር ጥቅም ለማዋል ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የጀመረው ስልጠናው በዛሬው ዕለት በሁሉም ክልሎች እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚሰጠውን ስልጠና በገለፃ ጀምረዋል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
