






በተፈጥሮ ችግር የተወለዱ ህፃናት የነፃ ህክምና እንዲያገኙ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተመም እንደተናገሩት በክልሉ በአፈጣጠር ችግሮች ምክንያት በማህበረሰቡ ውስጥ ተደብቀው ለማህበራዊና ለስነ ልቦናዊ ችግሮች የሚጋለጡ ማህበረሰብ ክፍሎችን በነጻ ቀዶ ህክምና ዙሪያ የሀይማኖት እና የሚዲያ ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የችግሩ ተጠቂ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስቀድሞ የመለየት ዘመቻ ከየካቲት 25-29/2017 ዓ/ም ድረስ እንደሚደረግ የገለፁት ኃላፊው በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ዘመቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚዲያና ከሀይማኖት ተቋማት በተጨማሪ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ኢብራሂም አያይዘውም እንደ ክልል በዚህ ዘመቻ የሚሰሩ የአፈጣጠር ችግሮች የእግር መቆልመም፣ የከፈር መሰንጠቅ እና የላንቃ መሰንጠቅ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ በረከት ኢዮብ በበኩላቸው ሲወለዱ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ እንዲሁም እግራቸው ቆልማማ ሆነው የተፈጠሩ ህፃናት ህክምና እንዲያገኙ ለማስቻል ሁሉም የሚዲያ ተቋማት ያላቸውን የሚዲያ አማራጮችን አሟጠው በመጠቀም ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጠይቀዋል።
አያይዘውም የሁሉም መዋቅር የሚዲያ ተቋማት ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን በወቅቱ ማስተላለፍ፣ አገልግሎቱን ለማሳለጥ ግንዛቤ የማስጨበጥ መልዕክቶችን መስራት፣ የመረጃ ቅብብሎሽ እና የሚዲያ ሽፋን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመድረኩ ለውይይቱ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው ጥልቅ ውይይትም ተደርጓል።
ችግሩ የሚስተዋልባቸው ህፃናት ጥቆማ እንዲያደርግ፣ የችግሩ ምንነት የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን የተፈጥሮ ክስተት መሆኑንና የህክምና አገልግሎት በማግኘት ችግሩ እንደሚስተካከል የግንዛቤ ስራው መሰራት እንደሚጠበቅም ተነግሯል።
ዘመቻው በዋናነት ነጻ ህክምና ዕድል ቆልማማ እግር ላላቸው ሚዛን አማን ማስተማሪያ ሆስፒታል የሚሰጥ መሆኑንና የላንቃና የከንፈር ስንጥቃት ላለባቸው አዲሰ አበባ ሙሉ ዘጪያቸው ተሸፍኖ እንደሚታከሙ፣ ግንዛቤ መፍጠርና ልየታ ማድረግ መሆኑም ተጠቁሟል።
ከዚህ ጎን ለጎን የማህ/ሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት እንዲያሳድሱ እና አባል ያልሆኑት አባል እንዲሆኑ የግንዛቤ ስራ በልዩ ትኩረት መሰራት ይጠበቃልም ተብሏል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለፁት የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ወገኖቻችን በስቃይና በህብረተሰቡ ዘንድ እየተሸማቀቁ ስለሚኖሩ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ወደ ህክምና ተቋማት በማምጣት የህክምና አገልግሎት በማግኘት ጤናቸው የተጠበቀ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
