




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ከJustice for all PF ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ሀገር በቀል እውቀት ለግጭት አፈታትና ዘላቂ ሠላም ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ የባለድርሻዎች ምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካኽዷል።
በክልሉ የህዝብ ልህዝብ ትስስር እንዲጎለብት በአርብቶ አደር አካባቢ የምግብ ዋስትና እንዲረጋጥ በመስራትና ሁሉን አካባቢዎች በመንገድ ማስተሳሰር፣ የጋራ ገበያ እንዲኖራቸው በማድረግ ዘላቂ ሠላም በመካከላቸው ማምጣት ያስፈልጋል ተብሏል።
ስልጠና ነክ ምክክሩ ጥልቅ ውይይት የተደረገ ሲሆን በዚህም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ የሚታየውን ዘረፋዎችና ተያይዘው የሚታዩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት እንዲቀረፍ መንግስታዊ ተቋማትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ተከታታይ ግንዛቤ እስከ ማህበረሰቡ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርበዋል።
ባህላዊ ተቋማትን መንከባከብ፣ እሴቶችን ማጠናከርና እውቅና መስጠት ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖረው የባህል አባቶችን እና የሀይማኖት ፎረሞችን ጠንካራ በማድረግ እነዚህ አካባቢዎች ላይ ጎልቶ የሚታየውን የጥሎሽ አሰጣጥ ባህል አቅማቸውን ያገናዘበ እንዲሆን ግንዛቤ ላይ መስራትና ተያይዘው የሚከሰተውን ዘረፋ መቀነስ አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።
በምክክሩ ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ተወካይና ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠለሞን ደነቀ ክልላችን የሚታወቀው በሠላማዊነቱና ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ነው ብለው ይኸውም ስራ የሚያበቃ ስላልሆነ ቀጣይነት ያለው ስራ ከሁላችሁም ይጠበቃል ብለዋል።
ኮንታ፣ ካፋና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች የሚገኙበት ድንበር አካባቢዎች ዙሪያ የሚታየውን ፀጥታ ክፍተቶች ለመፍታት የክልሉ ተቋማት በሚሰጡን ድጋፍ ትርጉም ያላቸውን መድረኮች ፈጥረን ውጤት አይተናል ያሉት የኮንታ ዞን ሠላም፣ጸጥታና ምልሻ መምሪያ ኃላፊ አቶ እስራኤል ጮንቄ ቀጣይ በቅንጅት ለመስራት ግብዓት ወስደናል ብለዋል።
ሀገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅመን እስካሁን የታዩትን ክፍተቶች ፈትተናል ያሉት የመኢኒት ጎልድያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጎንጥዮ ፋጂዮ በቀጣይም የሶስትዮሽ ኩታ ገጠም ምክክርና መግባባት መድረኮችን ፈጥረን የቀድመውን የተረጋጋና ልማታዊ ማህበረሰብ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
የጎባ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ታደሰ በበኩላቸው አርብቶ አደሮች በሚሰፍሩባቸው ዙሪያዎችም ክልል ከክልል፣ ዞኖች እና ወረዳዎች የጋራ ፎረምና ቅንጅት አጠናክረን ያልተቋረጠ ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
የኮንታ ኮይሻ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ማርቆስ ወንድሙ: በሰንሰለቱ ዙሪያ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት የሀይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎችና ባለድርሻ አካላት እርስ በርስ ተሳስረው በሚለሙበት ሁኔታ ላይ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
የኮንታ ኮይሻ ወረዳ፣ ከጎባ ወረዳና መኤኒት ጎልድያ ወረዳ ተወካይ የባህል አባቶች እንደተናገሩት ከልሉ ከተመሠረተ ወድህ የተለያዩ ህዝብ ለህዝብ መድረኮች ተፈጠረው ሠላምን የማስፈን ሥራዎች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
በመንግስትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለባህላዊ እውቀቶች እየሰጠ ያለው ትኩረት በየሰፈሩ የሚታየውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ያግዛል ያሉት አስተያየት ሰጪዎች: ቀጣይ የባህል አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች እና መላ ህብረተሰብ የጋራ ገበያ ከመፍጠር እስከ ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር እየመከርን ነው ብለዋል።
የመኤኒት ጎልድያ ተወካይ ወ/ሮ እታገኝ ሰዕድ በቀጠናው ዘላቂ ሠላም እና ልማት እንዲረጋገጥ ጠንክረው እንደሚሰሩ አመላክቷል።
በመጨረሻም ከሁሉም ብሔረሰቦች የተገኙ የስራ ኃላፊዎች፣ የጎሳ መሪዎችና ባለድርሻ አካላት በላ 7 አሀዝ የአቋም መግለጫ አወጥተው በቀጣይ በሚሰሩባቸው ነጥቦች ላይ መግባባት ፈጥሯል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
