
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በ1ኛ ሩብ ዓመት በማህበራዊ ዘርፍ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በርካታ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት የተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የክልሉን የትምህርት ስራ ውጤታማ ለማድረግ ከክልል እስከ ትምህርት ቤት ድረስ በርካታ የትምህርቱ ሴክተር የንቅናቄ ስራዎች መሰራታቸውን ነው አቶ አልማው የተናገሩት ፡፡
በሩብ አመቱ በክልሉ በዚህም ሂደት ከ5 መቶ ሺህ በላይ ከሚሆኑ ከትምህርት ማህበረሰብ የጋራ መድረክ ተፈጥሮ በትምህርት ዘርፍ ውጤት እንዲመዘገብ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉበት፣ኃላፊነት የወሰዱበትና የጋራ መግባባት መፍጠር የተቻለበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በክልልም ይሁን በሀገር ደረጀ ከተቀመጠው ከትምህርት ልማት ግቦች ዋነኛው የትምህርት ተሳትፎ ማሳደግ መሆኑን ያነሱት አቶ አልማው 965 ሺህ 284 ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ታቅዶ በየደረጃው በተደረገው ንቅናቄ 792 ሺህ 885 ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ በማምጣት የዕቅዱን 82 ፐርሰንት ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዘንድሮው ዓመት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ጥረት የተደረገበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሩብ ዓመት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ በውጤታማነት በማከናወን 2መቶ 2 ሚሊየን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ፣ በአይነትና በጉልበት መሰብሰብ መቻሉንና በዚህም በርካታ የመማሪያ ክፍሎችን መጠገንና የትምህርት ግብኣቶችን ለማሟላት ጥረቶች የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት ለትምህርት ስራ በየደረጃው ባለው በአስተዳደር እርከን የታለየ ትኩረት የተሰጠበትና ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት በመመደብ ማውረድ መቻሉን አመላክተዋል፡፡
የቅድመ አንደኛ ትምህርት አጠቃላይ ለትምህርት ጥራት ወሳኝና መሠረት በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አቶ አልማው በክልሉ 42 ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች እየተገነቡ እንዳለና እስከአሁን 26 ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው በጀት ዓመት 173 ሺህ 181 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ግብ ተጥሎ 141 ሺህ በመመዝገብ የዕቅዱን 82 ከመቶ ማሳካት የተቻለበት መሆኑንና በቅድመ አንደኛ ላይ ልዩ ትኩረት የመስጠት ውጤት ነው ያሉት ፡፡
የክልላችን ሁሉም ቀበሌዎች ውስጥ 888 ተጨማሪ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፍያ ጣቢያዎችን በማህበረሰብ ተሳትፎ ለመስራት ታቅዶ እስከአሁን ከ801 ተጨማሪ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መስራት መቻሉን አቶ አልማው አንስተዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
