





















ባለፉት ተከታታይ ወራት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’
በሚል አምድ ሥር አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የካፋ፣ የዳዉሮ፣ የቤንች ሸኮ እና የሸካ ዞኖችን አጠቃላይ ገጽታን የሚያሳዩ፤ የካፋ ባህላዊ ዱሞ ስርዓትና የዳውሮ ዱቡሻ ስርዓትን የቃኙ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡ አሁን ደግሞ የኮንታ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ህንግጫን እንቃኛለን፡፡ መልካም ንባብ!
የኮንታ ብሔረሰብ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችና ዕሴቶች ባለቤት መሆኑ እሙን ነው፤ ከእነዚህ ውብ ዕሴቶች አንዱ የሆነው የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ/ህንግጫ/ በዓል ነው።
የኮንታ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ /ህንግጫ/ በዓል በብሔረሰቡ ዘንድ በየዓመቱ በታላቅ ጉጉት ተጠብቆ የሚከበር ልዩ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ነው፡፡ ዕሴቱ ሳይጎድልና ውበቱ ሳይደበዝዝ እዚህ የደረሰ የብሔረሰቡ የማንነት መገለጫም ነው፡፡
ህንግጫ በኮንታ ብሔረሰብ አጠራር ያማረ፣ ያጌጠ፣ የለመለመ ማለት ሲሆን አደይ አበቦች ፈክተው የሚታዩበት፣ የክረምቱ ወራት አልፎ የጠራ ሰማይ የሚታይበት፣ አርሶ አደሮች የክረምት አዝመራቸውን አገባደው ከአረምና ኩትኳቶ ስራ አርፈው ለመልካም ፍሬ ተስፋ የሚሰንቁበት ወቅት በመሆኑ በብሄረሰቡ ዘንድ በልዩ ትኩረትና በተስፋ የሚከበር በዓል ነው።
የህንግጫ በዓል ሲከበር ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ እንደመሆኑ መጠን በዕለቱ ሁሉም ጠግበው፣ ጎዶሎው ሞልቶ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ የሚበላበት፣ ድሃ ከሀብታም እኩል የሚያከብርበት፣ መጥፎ ነገር ሁሉ ቀርቶ መልካም መልካሙ እንዲሸጋገር ፈጣሪውን የሚለምኑበት የጥጋብና ሙሉ የመሆን አስተምህሮ የሚገለፅበት የተስፋ በዓል ነው።
እንደ ባህሉ ትውፊት ህንግጫ ከጳጉሜ የመጨረሻዋ ቀን እስከ መስከረም 30 ድረስ ደምቆ ይከበራል። ከቤት እስከ ደጃፍ አካባቢ ይፀዳል፤ ከአዲሱ ዓመት የሚሻገር እድፍና ጉድፍ ይጠረጋል፤ ምድር ትዋባለች፡፡
ህንግጫ ከ12 ዓይነት በላይ የሆነው የኮንታ ባህላዊ ምግብ ተዘጋጅቶ የሚቀርብበት የባህል አውድም ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በዓል ማብሰሪያ እሳት የሚወጣው በጳጉሜ የመጨረሻዋ ቀን ነው፡፡
በህንግጫ ወቅት ‹‹ሙጬ ›› ማለት ከጳጉሜ 1 እስከ ጳጉሜ 5/6 ድረስ ያሉ ቀናትን የሚያመላክት ሲሆን በእነዚህ ቀናት ዉስጥ እህል ቢዘራ በተለይም ጤፍ ቢዘራ የማይበቅልና ቢበቅልም እንኳን ከግንዱ ተቆርጦ የሚወድቅና እንዲሁም ሳያድግ ቀጭጮ ስለሚቀር ወቅቱ ‹‹ ሙጬ ›› ተብሏል፡፡
የህንግጫ በዓል መቼና እንዴት ተጀምሮ እያደገ እንደመጣ ትክክለኛውን ጊዜ የሚጠቁም የጽሑፍ መረጃ ባይኖርም ከቀደምት አባቶች በአፈ-ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው የኮንታ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ማክበር የጀመረዉ በኦሞ፣ በጎጀብ እና በዝግና ተፋሰስ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደ ነበረ ነው፡፡
ይህም ኮንታ መንግሥት ተመስርቶ ግዛቱን ተቆጣጥሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም የመጀመሪያው የአራ የዘር ግንድ ቀዳሚ ንጉስ “ከካቲ ኤማዶ” ዘመነ መንግስት ከ12ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይበልጥ በተጠናከረ ሁኔታ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ ከጎረቤት ጋር በጋራ በመሆን በዓሉን እያከበሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሆኑ ታሪክና ባህል አዋቂ ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡
‹‹ህንግጫ›› ማለት እንደ ብሔሩ አባቶችና የታሪክ ምሁራን አገላለጽ የሁለት ቃላት የ‹‹ሂን›› እና የ‹‹ጊጫ›› ዉህድ ነዉ፡፡ ‹‹ሂን›› ማለት ወደዚያ አስፋ/ፊ ሲሆን ‹‹ጊጫ›› ማለት አሳምር፣ ጥረግ፣ አጽዳ፣ ፋቅ (Giid’ara) የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡
በመሆኑም ከዕለቱ በዓል ጋር የሚያያዝበት ምክንያት ጎረቤት በዓሉን አብሮ ለመታደም፤ ወጣቶች በበዓሉ ወቅት ለጭፈራ እና ለምርቃት ሲመጡ ባማረና ጽዱ በሆነ አካባቢ እንዲያከብሩ እንዲሁም በዓሉ ሲከበር እንግዳ ለመቀበል፤ ለመመራረቅ ከየጎረቤቱ አዲስ ዓመትን ለማክበር እና በአዲሱ ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከረሃብ ወደ ጥጋብ ሲሸጋገሩ ብሩህ ተስፋን ሰንቀዉ በእርቅና በጥጋብ ለምድሪቱ ሠላምን፣ በረከትን፣ ፍቅርን፣ ጤንነትን በመመኘት የሚቦርቁበት መሆኑን ያሳያል፡፡
አዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ አመልካች በመሆኑ ያንን ለማመልከት የተጠቀሙት ቃል ሲሆን ከበዓሉ ዝግጅት ጋር ይያያዛል፤ ይኸዉም ደጃፍ (Zabba) kariya Aassade Giic’c’aa፣ ለበዓሉ ከሚዘጋጅ የምግብ ዓይነቶች ዉስጥ አንዱ አንጮቴ ወይም Ushshushiya Giic’c’aa እና በበዓሉ ተዉቦና ደምቆ ለመታየት እንሶስላ ወይም wusoluwa Giic’aa ከሚለዉ ጋር የተያያዘ ነዉ፡፡
የኮንታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለዉ ሲሆን የዘመን አቆጣጠር የመጀመሪያ የመስቀል ወር / Mask’ala Aginaa / ይባላል፡፡
በህንግጫ በዓል አከባበር ወቅት ወጣቶች ከሚጫወቱት ጨዋታዎች ለአብነት “Hoyabee salo, wod’aassaa wosikkee , andoli bole, wohee baabo baabo, koole kooli godaa” ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህንግጫ በዓል እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ጎረቤት የተጣላ ሳይታረቅ ቂም በመያዝ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ስለሌለበት የተጣሉ ግለሰቦች በጎረቤት ሽማግሌ በተለይም በ’ሙጬ’ /በጳጉሜ/ ቀናት ይቅር ለእግዚአብሔር ይባባላሉ፡፡
ከቤት ርቆ ያለም ሆነ ከቤት ዉጭ ያለ ማንኛዉም የቤተሰብ አባል ወደቤት ሳይገባ ትርኳሽ ወይም “Ts’iifaa” ስለማይወጣና ዉጭ ከቀረ በዚያዉ ይቀራል ተብሎ ስለሚታሰብ የግድ ወደቤት ከገባ በኋላ ትርኳሽ ወይም “Ts’iifaa” በመያዝ እርኩስ መንፈስ ዉጣ እያለ ከዚህ በታች በተገለጸዉ መልክ ይፈፀማል፡፡
የትርኳሹን እጄታ በእጅ በመያዝ እና በማወዛወዝ ወደ ዉጪ የሚያወጣዉ አባወራ ለአዲሱ ዓመት ያደረሰዉን ፈጣሪ እያመሰገነና መጪዉ ዘመን የደስታ፣ የፍቅር፣ የጤንነት፣ የሠላም፣ የአንድነትና የጥጋብ እንዲሆን እየተማፀነ እቤት ዉስጥ ያለዉ የአሮጌዉ ዘመን ክፉ መንፈስ እንዲወጣ እያንዳንዱን የቤት ዉስጥ ቁሣቁስ መኝታዉን፣ መከታዉን፣ ምሰሶዉን፣ ወጋግራዉን፣ የከብቶችን በረት (ከበሬ ጫንቃ፣ ከላሞች ግት)፣ መዉጫ በሩን በትርኳሹ እየነካካ ‹‹የረሃብ የበሽታ የጥላቻ ክፉ መንፈስ ከዚህ ቤት ዉጣ›› እያለ ካዳረሰ በኋላ ትርኳሹን ከቤት አዉጥቶ ወደ ዉጪ አርቆ ይወረዉራል፡፡
ትርኳሹ (Ts’iifaa) በሚወጣበት ቀን በዕለቱ ለእራት የሚዘጋጅ ምግብ ማብሰያዉን ሞልቶ ይዘጋጃል፤ እንዲሁም በቤት ዉስጥ ያሉ የምግብም ሆነ የዉሃና የወተት ዕቃዎች ተሟልተዉ እና ተከድነዉ ማደር አለባቸዉ፤ ምክንያቱም እነኝህ ቁሳቁሶች ጎደሎ ሆነዉ የሚያድሩ ከሆነ ዓመቱን በሙሉ ችጋርና ርሃብ ከቤት አይወጣም ተብሎ ይታመናል፡፡
የዘመን መለወጫ በዓል ማብሰሪያ በአካባቢዉ ታዋቂ ወይም የዕድሜ ባለፀጋ በሆኑ አባቶች ቤት በመጀመሪያዉ ቀን በጋራ ይከበራል፤ በበዓሉ አከባበር ቀን የሚወጣዉ ትርኳሽ በችቦ መልክ ሣይሆን በምድጃ ዉስጥ አየነደደ ካለዉ የማገዶ ጉማጅ ከነፍሙ ተመዞ በመያዝ ይወጣል፡፡
የዚህ ጉማጅ ስም በአካባቢዉ አጠራር “ፂፋ” ይባላል፡፡ ከዚያም በኋላ የቤተሰቡ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸዉ ጎረቤቶች እንደየ ዕድሜያቸዉ ቦታ ቦታቸዉን ከያዙ በኋላ የእድሜ ባለፀጋ የሆኑ ከ1-3 በሚደርሱ ሽማግሌዎች ምርቃት ይደረጋል፡፡
ምርቃቱም፡- የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ቀርበው “ቦርዴ” በትልቅ እንስራ አሙልቶ በማፍሰስ በሴቶች እልልታ ታጅቦ ጠላዉን ለእያንዳንዱ ታዳሚ በማዳረስ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ከተሞላዉ እንስራ በዋንጫ የተቀዳ ጠላ በመጀመሪያ የተሰጣቸዉ የዕድሜ ባለፀጋዎች ይመርቃሉ።
በአሮጌዉ ዓመት ሲያጣላ፣ ሲያጋጨን የነበረዉ ክፉ መንፈስ ከመኃላችን ፈጣሪ ያርቅልን! ይህ ጠላ ሞልቶ እንደፈሰሰ ሁሉ ጤንነት ፍቅር ሠላም ጥጋብ በሀገራችን በአካባቢያችን በሰፈራችን እንዲሁም በእያንዳንዳችን ቤት እንዲዚህ ሞልቶ ይፍሰስ!
አዲሱ ዓመት የሕዝቡ እና የመንግስት አንደበት የሚጣጣምበት፣ ዘርተን የምንቅምበት፤ ወልደን የምንስምበት፤ ነግደን የምናተርፍበት፤ ከቤት የወጣዉ በሰላም የሚመለስበት፤ ያፈራነዉን በሰላም በፍቅር የምንበላበት ዘመን ያደርግልን! በአዲሱ ዓመት ስትወጡ እንቅፋት አይምታችሁ ስትናገሩ እዉነተኛ ሃሳብ አይጥፋባችሁ፤ ፍቅራችን እንደ ሰማይ ጉም እንደ ምድር ሰርዶ እንደ ጉንዳን ሕብረትና አንድነት እግዚአብሔር ያድለን! በመጨረሻም ከእኛ የተረፈዉን እግዚአብሔር ይመርቃችሁ በማለት ያጠቃልላሉ።
በፍቅር ከበደ
