


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2016 የምርት ዘመን የበጋ መስኖ ስንዴ የማብሰሪያ መርሀግብር የክልል አመራሮች እና የባለድርሻ አካላት በተገኙበት በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ተካሂዷል።
የክልሉ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በወረዳው ሜዳቦ ቀበሌ በ50 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እና የአከባቢው አርሶደአሮች ጋር በመሆን የበጋ መስኖ ስንዴ እርሻን አብስረዋል።
በክልሉ 7 ሺህ ሄክታር ማሳን በበጋ ስንዴ ለመሸፈን እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ከዚህም ውስጥ 50 ከመቶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግሯል።

የበጋ መስኖ እርሻ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር የአርሶአደሩን የስራ ባህል ቀይሯል ያሉት አቶ ማስረሻ በአመት አንድ ጊዜ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነው የእርሻ ስራ አሁን በመስኖ እርሻ እምርታ እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ማስረሻ አክለው የክልሉን የመልማት አቅሞች አሟጦ በመጠቀምና በቴክኖሎጂ በተደገፈ የግብርና ተግባር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ቁርጠኝ አቋም እንዳለውም አስረድተዋል።
ዞኑ በተፈጥሮ የተቸረውን ፀጋ ወደ ሀብት በመቀየር የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር ተስፋ ሰጪ መሆኑ የገለጹት የካፋ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አጥናፉ ሀይሌ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ዓለሙ በበኩላቸው የግብርና ስራን በሜካናይዘሽን በማስደገፍና አርሶ አደር አሳታፊ ምርጥ ዘር በማባዛት የክልሉን የምርጥ ዘር ፍላጉት በመመለስ ምርትንና ምርታማነት ለማሳደግ ተቋሙ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጨረሻም የክልል አመራሮቹ እና የባለድርሻ አካላት በወረዳው በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
