ፓርቲያችን ብልፅግና ትላንት የሥርዓተ መንግስት አስተዳደራችን አንድ አካል ሆነው ካለፉ ልንቀይራቸው ከማንችላቸው ታሪኮች ጋር ፈፅሞ ፀብ የለውም፡- አቶ አደም ፋራህ

Spread the love

ፓርቲያችን ብልፅግና ትላንት የሥርዓተ መንግስት አስተዳደራችን አንድ አካል ሆነው ካለፉ ልንቀይራቸው ከማንችላቸው ታሪኮች ጋር ፈፅሞ ፀብ የለውም ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

ፓርቲው በመርህ ደረጃ ከትላንት ተምሮ፣ ዛሬን አሳምሮ፣ ነገን የተሻለ ማድረግን በማመን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በመትጋት ላይ እንደሚገኝ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

የብሔራዊ ቤተመንግስት እድሳት አቧራን አራግፎ አሻራን የማኖር ስራም በዚሁ እሳቤ የተቃኘ ነው ሲሉም አክለዋል።

ጥበብ እና ኢትዮጵያ፤ ስልጣኔ እና ኢትዮጵያ፤ ኅብረ-ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያ፤ ቀደምትነት እና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የሆኑ በልኳ ተሰፍተው ስሟ ሲጠራ አብረው የሚነሱ ተቀፅላዎቿ መሆናቸውን በስፍራው የተሰደረው መኪናውም፣ የንግስና ካባውም፣ ዙፋኑም እና የተለያዩ የሀገራችንን አካባቢዎች የሚገልፁ ስጦታዎችና ሌሎች መገለጫዎች ይመሰክራሉ ብለዋል።

ትላንት ታሪክ ነው፤ ዛሬ ቅርስ ነው፤ ነገ ውርስ ነውና እይታችንን ልዕልና መር ጉዞ ላይ በማድረግ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንትጋ ብለዋል አቶ አደም ፋራህ በመልዕክታቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *