



አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተግባሩ እየተመራ እንዳለም የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
በዳዉሮ ዞን የታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል በተለያዩ የሕክምና ዓይነቶች በሰለጠኑ ባለሙያዎች አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ከሆስፒታሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በተለይም በማህጸንና ጽንስ፣ በሕጻናት፣ በአጥንትና ድንገተኛ አደጋዎች፣ በአጠቃላይ ቀዶ ጥገናና በውስጥ ደዌ በሽታዎች በስፔሻሊት ደረጃ የሕክምና አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል።
ከእነዚህ አንዱ በሆነው በማኅጸንና ጽንስ ስፔሻሊት ደረጃ የማኅጸን ውልቃትና መንሸራተት በሳብ ስፔሻሊት ደረጃ መሰጠት መጀመሩ የብዙ እናቶችን ሞትና ስቃይ መቀነስ እንደቻለም ተገልጿል።
ጠቅላሉ ሆስፒታሉ ከማኅጸንና ጽንስ ጋር በተያያዘ በሣምንቱ ከ10 በላይ የቀዶ ጥገና ከሚያደርጋቸው እናቶች መካከል ከ6 ያላነሱ እናቶች የማኅጸን ውልቃትና መንሸራተት ያጋጠማቸው እናቶች መሆናቸውን የማኅጸንና ጽንስ ሳብ ስፔሻሊስት ዶክተር ወንድምገኘሁ ሲሳይ ተናግረዋል።
በሽታው ብዙ ልጆችን በሰለጠነ ባለሙያ ሳይታገዙ በምጥ በሚወልዱ እናቶች፣ ዕድሜኣቸው በገፋ እናቶችና ከባባድ የጉልበት ሥራ አዘውትረው የሚሠሩ እናቶችን በብዛት እንደሚያገጥም ነው የገለጹት።
የማኅጸን ውልቃትና መንሸራተት ያጋጠማቸው እናቶች ላይ ማኅበራዊ መገለልም ሊደርስባቸው ስለሚችል በማናቸውም አጋጣሚ ከማኅጸን ጋር ተያይዞ የሚታመሙ እናቶች መመርመርና ራሳቸውን ከስቃይ ሊታደጉ እንደሚገቡም ዶክተር ወንድምገኘሁ ተናግረዋል።
ውልቃቱ ያጋጠማቸው እናቶች ከሚደርስባቸው ስቃይ ራሳቸውን የማግለልና ባሎቻቸው ሌላ ሚስት እንዲያገቡ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ከሕመምተኞቹ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳይም ገልጸዋል።
አንዳንድ እናቶች ለረዥም ዓመታት በሕመሙ እንደሚሰቃዩ የገለጹት ዶክተር ወንድምገኘሁ እነዚህን እናቶችን ለመታደግ በተቀናጀ ርብርብና ጥረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አሁን በቁጥር በርካታ እናቶች ወረፋ ይዘው እየተጠባበቁ ሲሆን ከሚደርስባቸው ስቃይ ለመታደግ የእናቶች ለመታከም የሚያስችላቸው የኢኮኖሚ እጥረት፣ ተጨማሪ የማኅጸንና ጽንስ ሐኪም ያለመኖር፣ የሕክምና ግብአት ውድ መሆንና አንዳንዴ በገበያ አለመገኘታቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
የጠቅላላ ሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያዕቆብ ሌንጮ ከእናቶች ጋር ተያይዞ እየተሰጠ ባለው ሕክምና ወደ ሌላ ቦታ ለተሻለ ሕክምና የሚሸኙ እናቶች ቁጥር መቀነሱን ገልጸዋል።
አልፎ አልፎ በደም እጥረት ብቻ የሚሸኙ እናቶችንም ለማስቀረት ከደም ባንክ በተቀናጀ ርብርብ በመሥራት እናቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከማኅጸንና ጽንስ ጋር ተያይዞ ጠቅላላ ሆስፒታሉን ተመራጭ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
የዳዉሮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት ቸርነት በበኩላቸው ጠቅላላ ሆስፒታሉ ለዞኑ፣ ለኮንታ ዞንና ኦሮሚያ አጎራባች ወረዳዎች አገልግሎቱን በተሻለ ሁኔታ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይህንን የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና ተደራሽነትን በማስፋት በተለይም በማኅጸን ውልቃትና መንሸራተት ያጋጠማቸውን እናቶች ከስቃይ ለማዳን የሚያስችል ሥራ በቀጣይም እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ለዘርፉ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንና በየቤታቸው ስቃዩን ደብቀው እየተወጡ የሚገኙ እናቶች ወደ ጠቅላላ ሆስፒታሉ ቀርበው ታክመው እንዲድኑም ጥሪ መቅረቡን ደሬቴድ ዋካ ቅርንጫፍ ዘግቧል።
