የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ሚና እንዲጎለበት የሴቶች ኮከስ አደረጃጀት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሴት ተመራጭ ኮከስ አባላት ከክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በኮከሱ ማስፈፀሚያ መመሪያ እና እስከአሁን አፈፃፀም ላይ በቦንጋ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ምክትል አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሀይ ደርጫ እንደ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ ተግባር ደንብ ወጥቶለት ወደ ስራ ከተገባ ጊዜ ጀምሮ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ በማስቀረት ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ሚና እንዲጎለበት የሴቶች ኮከስ አደረጃጀት ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።

ሴቶች በሁሉም መድረክ ንቁ ተሳታፊና ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው እንዲከበር የሴቶች ኮከስ አደረጃጀት ትልቅ ሚና እንዳለውና ለዚህም በታችኛው መዋቅር ደረጃ የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ለተግባሩ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ክብርት ወ/ሮ ፀሀይ አሳስበዋል።

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ኮከስ ተባባሪ አባል ወ/ሮ ለምለም አምሳሉ፤ የክልሉ ምክር ቤትና የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሴቷን በሚመለከት ሰፊ ስራዎችን በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረው ቢሮው ሴቷን ተጠቃሚ ለማድረግ በልማት ማህበር አደራጅቶ ስራውን በንቅናቄ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ሴቶችን ሁሉአቀፍ ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ የሴቶች ልማት ህብረት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ የገለጹት ወ/ሮ ለምለም ለዚህም ሴት የምክር ቤት ተመራጭ አባላት ሴቶችን ከማደራጀት እና ከመደገፍ አንፃር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመቀናጀት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት የሴት ተመራጭ ኮከስ አባላት ሰብሳቢ ወ/ሮ አሚና ሀሰን በበኩላቸው የክልሉ ሴት ተመራጭ ኮከስ አባላት አጠቃላይ ለመስራት የታቀዱ ተግባራትን በተሻለ አቅም እያከናወነ መሆኑን ገልጸው በዚህም ሴት የምክር ቤት አባላት የመረጣቸውን ህዝብ የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በመድረኩ የሴቶች ኮከስ ማስፈፃሚያ መመሪያ እና የኮከሱ እስከአሁን አፈፃፀም የቀረበ ሲሆን በቀረቡት ሰነዶች መነሻ የኮከሱ አባላት በተነሱ ጉዳዮች ላይ ውይይትና የጋራ ሀሳብና አስተያየት በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል፡፡

የሴት ተመራጭ ኮከስ አባላት በማስፈፀሚያ መመሪያና አፈፃፀም የምክክር መድረክ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሀይ ደርጫን ጨምሮ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ሴት የምክር ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *