





የጤና ሚኒስቴር ሱፐርቪዥን ቡድን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዳውሮ፣ ኮንታና ካፋ ዞን ገወታ ወረዳ ያካሄደውን ሁለተኛ ዙር የድጋፍና ክትትል ስራዎችን አጠናቋል።
የሱፐርቪዥን ቡድኑ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ሁሉ አቀፍ የወባ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም መደበኛ የጤና ተግባራት ስራዎች ተጠናክሮ ልቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል።
በክልሉ ያለውን መሠረታዊ የጤና አገለግሎት አሰጣጥ ደረጃ ማረጋገጥና በጋራ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ መግባባት መፍጠር መቻሉንም የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስረድተዋል።
ከመረጃ ጥራት ጋር ያለው ክፍተት በልዩ ትኩረት ተሰርቶ በአፋጣኝ ልስተካከል ይገባልም ተብሏል።
የማህበረሰቡን ጤና መጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን የጠቀሱ ዶ/ር ጌታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበረሰቡን የጤና ችግር ለመፍታት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
ኢንጂነር ታደሰ የማነ የጤና ሚ/ር የመሰረተ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ በክልሉ የጤና ስራዎች እንዲጠናከሩ መንግስትና ፓርቲው እየሰጠ ያለው ትኩረትና የጤና ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች ተደጋግፎ የመስራት ልምድ ለሌሎች አከባቢዎች ምሳሌ የሚሆን እንደሆነ አብራርተዋል።
የሱፐርቪዥን ቡድኑን መርተው እስከ ጤና ኬላዎች ድረስ የተንቀሳቀሱ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው በድጋፍ ወቅት የተለዩ ክፍተቶችን ለማረምና በጥንካረ የታዩ አፈፃፀሞችን ለማስቀጠል እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በዘመቻ እየተከናወኑ ያሉ ጠንካራ የወባ መከላከያና መቆጣጠሪያ ስራዎች በትከክለኛ የመረጃ ስራ እንዲደገፉ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተገልጿል።
ለጤና ፕሮግራሞች የሚመደቡ በጀቶችና ቁሳቁሶች ለታችኛው መዋቅር ወርደው በተለይ ለወባ መከላከልና መቆጣጠር ዘመቻ እንዲውሉ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ኢብራሂም አስረድተዋል።
በተለይ የጤና መረጃዎች ትክክለኛነት፣ ታኣማንነትና ወቅታዊነት እንዲጠበቁ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል።
የወባ መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች እና ሌሎች የጤና ተግባራት መረጃዎች ህብረተሰቡን በተገቢው እንዲደርሱ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ጋር የሚሰሩ ስራዎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ታውቋል።
ክልሉ አዲስ ከመሆን ጋር በተያያዘ የማስተዋለውን የጤና መሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለመሙላትና ደረጃቸውን የጠበቁና በግብአት የተሟሉ የጤና ተቋማትን ለመገንባት የጤና ሚኒስቴር መስራያ ቤት ክልሉን በልዩ ሁኔታ እንዲደግፍ ተጠይቋል።
የጤና ሚኒስቴር የሱፐርቪዥን ቡድን በክልሉ እስከታችኛው የጤና መዋቅር ድረስ ስላደረገው ረዥምና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ተግባራት የጤና ቢሮ ሀላፊ በአቶ ኢብራሂም ምስጋና አቅርበዋል።
