






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በ2016 በክልሉ በመንግሥትና አጋር አካላት የተሰሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን የሚያስቃኝ የፎቶግራፍ ኢግዚቢሽን በታርጫ ከተማ አካሂዷል።
የፎቶግራፍ ኢግዚቢሽኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢንጂነር)፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ተሳታፊዎች ጎብኝቷል።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ለጎቢኚዎች ገለጻ አድርገዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ መንግሥትና በልማት አጋር ድርጅቶች ከ1 ቢሊዮን አምስት መቶ ሚሊዮን ብር በሆነ ሀብት በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች የተገነቡ በቁጥር 89 ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ያብራሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ የሺዋስ በዚህም ከ1.2 ሚሊዮን የሚበልጥ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን የልማት ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት አቶ የሺዋስ በበጀት ዓመቱ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በአስተዳዳራዊ ዘርፎች መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የጠቆሙት።
በክልሉ በተላይም በአርብቶ አደርና ቆላማ አከባቢዎች በመንገድና ድልድይ ግንባታ እንዲሁም በመስኖና ንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተሰሩ ውጤታማ ተግባራት የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ተግባራት አውንታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በልማት ሥራዎች ከፍተኛ የህብረተሰብ ተሳትፎ መኖሩን የገለጹት አቶ የሺዋስ በቅርብ ጊዜያት ግንባታቸው ተጠናቆ ለህብረተሰብ አግልግሎት ክፍት የሚሆኑ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።
አውደርእይ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የተሰሩ አንኳር የልማትና መልካም አስተዳደር፣ የንቅናቄ፣ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ተግባራት በዝርዝር በፎቶ መልክ ሰነዶ የያዘ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በዕድገቱ በዛብህ
