















በተገባደደው በጀት ዓመት በክልሉ መንግስት ታቅደው የተከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን የምክርቤት አባላት አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡
በክልሉ የተሻለ ኢንቨስትመንት ፍሰት የመኖሩን ያህል በዘርፋ የተሰማሩ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንቱ ባለበት አካባቢ ምን አስተዋጽኦ አበርክተዋል የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል ፡፡
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር የሚስተዋለውን የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርበት ዕጥረትን ከመቅረፍ አንጻርና አሲዳማ አፈርን ከማከም አንጻር አሁንም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የምክርቤት አባላት ጠይቀዋል ፡፡
አባላቱ በመንግስት የተነደፋ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የተሻሉ የመሆናቸውን ያህል ክፍተት የታዩባቸው ላይ መንግስት ትኩረት በማድረግ ሊሰራባቸው ይገባል ሲሉም አስተያየት በመስጠትና ጥያቄዎችንም ለአስፈጻሚው ተቋማት አቅርበዋል ፡፡
የምክርቤት አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ውስጥ በመንገድና መሰል መሰረተ ልማቶች አፈጻጸም የተሻለ ቢሆንም በፌደራል መንግስት በኩል የተያዙ ለአብነትም ከቦንጋ አመያ ፣ ከሺሾንዴ ቴፒ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት እና ከኢሳራ ዋካ የአስፓልት መንገድ መበላሸትና ዘላቂ ለምን እልባት አልተሰጣቸውም ? የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል ፡፡
የጤና ስራዎች አፈጻጸም ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል ፡፡
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በርካታ ስራዎች የመሰራቱን ያህል አሁን ላይ ለክልሉ ስጋት ሆኖ የቀጠለውን ይህንን በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ስራ ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሁም የምክርቤት አባላት ድርሻቸውን ወስደው ሊሰሩ እንደሚገባ ተነስቷል ፡፡
የወባ በሽታ መድሐኒት በመንግስት ጤና ተቋማት የማይገኙበትና በግል ጤና ተቋማት መኖራቸው መንግስት ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡
የነዳጅ አቅራቢ ማደያዎች አካባቢ ያለው ያልተስተካከለ አሰራር የመልካም አስተዳደር ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል ፡፡ የቁጥጥር ስርዓቱ ምን ያህል እየተመራ ነው? የሚል ጥያቄም ከምክር ቤት አባላት ተጠይቋል ፡፡
በገጠር መንገዶች አተገባባር የተሻሉ አፈጻጸሞች የመኖራቸውን ያህል በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ የሚበዛባቸው አካባቢዎች በተለይም ቄኔች በተባለ ቦታ ተደጋጋሚ አደጋ የሚበዛበት በመሆኑ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ስሉም የምክርቤት አባላት ጠይቀዋል ፡፡
የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አንጻር በርካታ ሀብቶች ተሰብስበው ገቢ አለመሆናቸው ምክንያቱ ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል ፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ከምክርቤቱ አባላት አስተያየት ተሰጥቷል ፡፡
ክልሉ በግብርና ልማት ስራዎች ትልቅ አቅም እንዳለው የሚታወቅ ቢሆንም ግብርናውን ለማሸጋገር አሁንም በዘርፋ ያሉ ተቋማትን አቅም በማሳደግ በኩል ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል ፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች አርሶ አደሩ የሚያመርታቸውን ምርቶች በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የገበያ ትስስሩ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል ፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ግንባታቸው በተለይም ረዥም ዓመታትን ያስቆጠሩ በተገቢው ተለይተው ከመልካም አስተዳደር ችግርነት የሚሸጋገሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባልም ተብሏል ፡፡
በድልድይ ግንባታዎች በኩልም በየአካባቢው ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተነስቷል ፡፡
በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተለይም የጎባ አካባቢዎችን በልማቱ ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ትኩረቱ አነስተኛ ነው በማለት የምክርቤት አባላት ጥያቄ አንስተዋል ፡፡
የናኦና ጫራ አካባቢ ልጆች በአርብቶ አደሩ የትምህርት ፕሮግራሞች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ፡፡
የህብረት ስራ ማህበራትን ከማጠናከርና ከመደገፍ አኳያ ያለው አፈጻጸም አነስተኛ መሆን ማህበራት በሚፈለገው የዕድገት ደረጃ እንዳይሻገሩ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል ፡፡
መንግስት ትኩረት ከሰጠባቸው ተግባራት የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ማስመለስ ስራ አንዱ ሲሆን ይህም ስራ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ተጠናክሮ ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል ፡፡
በትምህርት ለትዉልድ የተሰራዉ ስራ የሚበረታታ ሲሆን
የተማሪን ዉጤት ለማሻሻል አሁንም ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል።
የስራ ዕድል ከማመቻቸት አኳያም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ከምክርቤት አባላት በጥያቄ ቀርቧል ፡፡
በንጹህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ጥሩ ስራዎችመሰራታቸዉን ጠቅሰዉ በአንዳንድ አካባቢዎች ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል ፡፡
ቱሪዝምን ከማስፋፋፈት አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም በአስተያየታቸው ገልጸዋል ፡፡
በመስኖ ልማት አውታሮች የተጀመሩፕሮጀክቶች ክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሚናቸው ትልቅ በመሆኑ በጥናትና ዲዛይን ስራዎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ከፍጻሜ እንዲደርሱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡
የኤች አይቪ ኤድስ ጉዳይ አሁንም ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ የዘርፉ አመራሮች በትኩረት ሊሰሩበት ይገባልም ተብሏል ፡፡
ጽዱ ኢትዮጵያን የመፍጠር፣ የከተማ ኮሪደር ልማት ስራዎች ፣ የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ አስደግፎ የመስጠት ዝንባሌዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የምክርቤት አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡
በከተሞች የደረቅ ቆሻሻና የፍሳሽ ቆሻሻዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ የሚወገዱበት አሰራር ተጠናክሮ ሊሰራበት አንደሚገባ አባላቱ በጥያቄ አንስተዋል ፡፡
በታጠቅ አበበ
