




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ፣በፍቃደኝነት ግብር የመክፈል ባህል እንዲዳብር ለማስቻል ያለመ የባለድርሻ አካላት ምክክር በሚዛን አማን ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ፥ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በማሻሻል የገቢ አቅምን ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ የሚዲያና ኮሚውኒኬሽን ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ አደረጃጀቶች በገቢ አሰባሰብ ረገድ ግንዛቤ በመፈጠር የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱም ወ/ሮ ህይወት ያብራሩት።
በክልሉ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚቻልበት ዋንኛው መሳሪያ ከግብርና ታክስ በሚገኝ ገቢ ወይንም የፋይናንስ ወረት መሆኑ የጠቆሙት ሀላፊዋ ይህን ደግሞ ግብር ከፋዩ አምነው ግብሩን ስከፍል መኾኑን አንስተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 9.7 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የክልሉን መንግስት ወጪ 60 በመቶ መሸፈን መቻሉን የገለጹት ወ/ሮ ህይወት በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ 18.4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የክልሉን መንግስት ወጪ 64.5 በመቶ ለመሸፈን እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዜጎች ግብይት ስፈጽሙና አግልግሎት ስያገኙ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል እንዲያሳድጉ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ግንዛቤ መፈጠር እንደሚገባም ወ/ሮ ህይወት አሳስበዋል።
ተሞክሮዎች በማስፋት እንዲሁም በገቢ አሰባሰቡ አደረጃጀትን በተገቢው መጠቀም እንደሚገባ የገለጹት በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግርማ ባሻ በየጊዜ ውጤታማነት በመገምገም አፈጻጸሙን ማሻሻል ይግባል ብለዋል።
ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር እንዲሁም ችግር ፈቺ ድጋፋዊ ክትትል ስረዓት በመዘርጋት የገቢ አሰባሰቡን ማሳለጥ እንደሚገባም ነው አቶ ግርማ ያስገነዘቡት።
በመድረኩ የተገኙ የባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ተግባሩን በተሻለ መልኩ ለመፈጸም ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸው በየደረጃው ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
ስልጠናው በግብር አስተምህሮ ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ የፈጠረ መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ በቀጣይ ለተግባሩ ውጤታማነት በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
