
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የኢሬቻ በዓል ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነትና ይቅር ባይነት የሚፀናበት ታላቅ ባህላዊ እሴት መሆኑን ገለጹ።
አቶ ፍቅሬ ይህንን የገለጹት ለመላው የኦሮሞ ህዝብና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የእንኳን ለኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት ነው።
በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ የክረምቱን የጨለማ ወቅት አልፎ ወደ ብርሃን ዘመን በሰላም ላሸጋገረው ፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ታላቅ የደስታ መገለጫ መሆኑን ኃላፊው በመልዕክታቸው አንስተዋል። ኢትዮጵያ በብዝሃነትና በውብ ባህሎች የደመቀች ሀገር እንደመሆኗ፣ ኢሬቻ ከበርካታ እሴቶቿ መካከል አንዱና ዋነኛው እንደሆነም አስረድተዋል።
አቶ ፍቅሬ አክለውም “ኢሬቻ ቂም በይቅርታ የሚሻርበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ጥላቻ ቦታውን አጥቶ ወንድማማችነትና አብሮነት የሚነግስበት ታላቅ ባህላዊ መድረክ ነው” ሲሉ የበዓሉን ማህበራዊ ፋይዳ አስረድተዋል።
የኢሬቻ በዓል ከባህላዊ እሴቱ ባለፈ ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማነፅ ረገድ አይነተኛ ሚና እንዳለው የገለጹት አቶ ፍቅሬ፣ በዓሉ ለቱሪዝም መስህብነትና ለኢኮኖሚ ምንጭነት በማገልገል ለሀገራዊ ብልጽግና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም፣ ሁሉም ዜጋ የኢሬቻን አስተምህሮትና እሴቶች ተግባራዊ በማድረግ ለሀገር ግንባታ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊው፣ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
