ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል የፀጥታ ስጋት ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

የኢፌዴሪ የሠላም ሚኒስቴር፤ “ሠላምን በማጽናት በልማት ማንሰራራት” በሚል መርህ ቃል ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሠላምና ፀጥታ መዋቅር የባለድርሻ አካላት ስልጠና በሚዛን አማን ከተማ እየሰጠ ይገኛል።

በመድረኩ ክልላዊ የሠላም ሁኔታ አዝማሚያ ሰነድ በክልሉ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ምክትል የቢሮ ሀላፊና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ ቀርበው ሰፊ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የመድረኩ ተሳታፊዎቹ በክልሉ የፀጥታ ስጋት ምንጮችን በመለየት ቀደመው የመከላከል ስራ በቅንጅት መከናወን እንዳለበት አንስተዋል።

ክልሉ ከጎረቤት ሀገር እንዲሁም ከሌሎች ክልሎች ጋር በሚዋሰንባቸው ቀጠናዎች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፀጥታ ስጋቶች መኖራቸውን ያነሱት ተሳታፊዎቹ፥ ይህንንም በትኩረት በመከታተል ሰላም ማስፈን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአርብቶአደር አከባቢዎች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር ተያይዘው የሚስተዋል ተደጋጋሚ ግጭቶች መኖራቸውን ያነሱት ተሳታፊዎቹ፥ ይህንንም ችግር ተከታታይነት ባለው ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በህግ ማስከበር መግታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ግጭት ተፈጥሯዊ ክስተት ቢኾንም ግጭትን በአግባቡ ማስተዳደርና ችግሮችን በዘላቂነት በውይይት መፍታት እንደሚገባ የገለጹት ተሳታፊዎቹ ሁሉም ኅብረተሰብ ለሠላም መስፈን በባለቤትነት መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በአርብቶአደር ቀጠና የሚስተዋለው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ከወሰን ተሻጋሪ የፀረ ሠላም ሀይሎች ጋር የሚገናኝ በመኾኑ የህግ ማስከበር ስራው እንዲጠናከርም አሳስበዋል።

በአንዳንድ አከባቢዎች ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ያለው ማነቆ ለፀጥታ ስራው ማነቆ መኾኑን ያነሱት የመድረኩ ተሳታፊዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥም በአጽንኦት ጠይቀዋል።

ድንበር በሚዋሰኑ አከባቢዎችና ከአዋሳኝ ክልሎች ጋር የተጀመረው የጋራ ፎረም ውይይት መጠናከር እንዳለበት ያሳሰቡት ተሳታፊዎቹ ለፀጥታ መዋቅር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችም እንዲመቻች ጠይቀዋል።

ሠላምና ልማት እርስበርስ የሚተሳሰር በመኾኑ የአከባቢን ሠላም በማረጋገጥ ልማትን ማስፋፋት እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን ለገብራዊነቱ ሁሉም ኅብረተሰብ በባለቤትነት እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *