ሪፖርታዥ

Spread the love

የህብረተሰብ ተሳትፎን በማላቅ በከተሞች የተጀመሩ ስራዎችን ከግብ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ የከተማ አስተዳደሮች ገለጹ

ከተሞች ለነዋሪዎች ለመኖሪያ ምቹና ፅዱ እንዲሆኑ የተለያዩ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት እየተከናወኑ ነው፤ ለውጥም እያመጡ መሆናቸውን የቴፒ፣ማጂ-ቱም እና ጪዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ገልጸዋል።

በመሆኑም የህብረተሰብ ተሳትፎን በማላቅና ቅንጅታዊ አሠራሩን ማጠናከር በከተሞች የተጀመሩ ስራዎችን ከግብ ለማድረስ ወሳኝ መሆኑን ከንቲባዎች ጠቁመዋል ።

ቴፒ ፣ ማጂ ቱም እና ጪዳ ከተማ አስተዳደሮች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት በሸካ ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ኮንታ ዞኖች ከሚገኙ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ሦስቱም ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች በተለያየ ጊዜ የተመሠረቱ ከተሞች ሲሆኑ እነዚህን ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለአልሚዎች ሳቢ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

የቴፒ ከተማ አስተዳደር በክልሉ ከሚገኙ ብዝሃ-ማዕከል ከተሞች አንዱና በ6560 ሄ/ር ይዞታ በ3 ከተማ ቀበሌ ተዋቅሮ የሚገኝ ከፀጥታ ችግር በመላቀቅ ወደ ፈጣን የልማት ግስጋሴ ላይ የሚገኝ ከተማ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ለገሠ አስረድተዋል ።

ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹና ተወዳዳሪ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑን የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ያሬድ ለገሠ ገልጸዋል ።

በሸካ ዞን፣ ከቴፒ ከተማ አስተዳደርና ከማዘጋጃ ቤት በተመደበው 48 ሚሊዮን ብር በጀት የተለያዩ የአካፋይ መንገድ፣ አረንጓዴ ልማት አካባቢ ፣ መልሶ የማልማት፣ የእግረኛ መንገድ፣ ወሰን የማስከበር፣ የፈሳሽ ማስወገጃና ሌሎች ስራዎች እየተሰራ ከመሆኑም በላይ የአካፋይ መንገድን በዲምላይት የማስዋብ፣ የፋውንተንና የፈሳሽ ማስወገጃና ሌሎች ስራዎችን ለመስራት በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን አቶ ያሬድ ተናግረዋል ።

የህብረተሰብ ተሳትፎን ከማረጋገጥ አንጻር 5.5 ሚለየን ብር ከህብረተሰብ ተሳትፎ በተገኘው 2.3ኪ.ሜ የቴፒ አውሮፕላን ማረፊያ የዙሪያ አጥር መታጠሩን፣ ከ10 ሚለዮን ብር በላይ የጎጂ ወንዝ ድልድይ ተገንብተው አፈፃፀሙ 92% መድረሱ ለአብነት በመጥቀስ እንዲሁም ሌሎች አመርቂ ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ እንደሆነ አክሏል ።

ከተማውን መልሶ ከማልማት በከተሞች ዋና ዋና መንገዶች ያረጁ 22 ቤቶችን ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየትና በመግባባት ፈርሶ አዳዲስ ህንፃዎች ግንባታ መጀመሩን አንስተዋል።

ሳይፈቀድ የተያዙ ይዞታዎችን ወደ ህጋዊ መስመር በማስገባት የከተማ ፕላን ጥሰትን ለማስቀረት በተሰራው ስራ በከተማው ከሚገኘው 2319 ይዞታዎች ውስጥ 1479 የፕላን ስምምነት ያላቸውን በመለየት ከነዚህ ውስጥ 647 የመሬት ማረጋገጫ ካርታ የተሰራላቸው መሆኑን በመግለፅ ቀሪዎቹን በአዲሱ በሚሰራው በከተማ በስትራክቸራል ፕላን ምላሽ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል ።

መሬትን በሊዝና በምደባ ለመኖሪያ፣ ለደርጅትና ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ከማዘጋጀትና ከማስተላለፍ 6ሄ/ር ወይም 124 ፕሎት ለመኖሪያ፣ 5 ለተደራጁ ማህበራት፣ 6 መሬት ለኢንቨስትመንት ማስተላለፍ መቻሉን አቶ ያረድ ገልጸዋል ።

የከተማውን ጽዳትና ውበት ለማስጠበቅ የቆሻሻ ማንሻ መኪና ባለመኖሩ ለስራው ማነቆ ሆኖ መቆየቱን በማንሳት ችግሩን ለመፍታት ግዥ ለመፈፀም በበጀት መደገፉን ጨምረው አንስተዋል ።

መንገድ ለአንድ ከተማ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት ከሦስቱም አቅጣጫ የተጀመሩ የፌደራል የአስፓልት መንገዶች ከከተማው የሚጀመርበት ሂደቱን የሚመለከታቸው አካላት እንዲያመቻቹና የተለያዩ የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ አልሚዎች በከተማይቱ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እንዲያለሙ ጥሪውን አቀርበዋል ።

የማጂ-ቱም ከተማ ዕድሜ ጠገብ ከተማ እና በቆይታው ልክ ያልለማ በመሆኑ ለከተማዋ የሚመጥን የከተማ መሠረተ ልማት ለማሟላት ሰፊ ሥራዎች በቅንጅት እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት የማጂ ቱም ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እሸቱ አየለ ናቸው።

በከተማው መልሶ ማልማት በተለያዩ መንደሮች 28 የቀበሌ ቤቶችን በማንሳት ለተነሱት ነዋሪዎች ሳይፈናቀሉ ሌላ መኖሪያ ቤቶችን በማመቻቸት 8 ዘመናዊ ህንፃዎች በባለሀብቶች ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ያሉት መኖራቸውን ከንቲባው አንስተዋል።

በከተማው 155 ሳይፈቀድ ከተያዙ ይዞታዎች ዉስጥ 60 የፕላን ስምምነት በመኖሩ ካርታ መሰጠቱንና 95 በማስፋፋት የተያዙ በመሆናቸው ወደ መሬት ባንክ መመለሱን ገልጸዋል።

በከተማው ለተለያዩ አገልግሎት የሚሆን መሬት ከማቅረብ በ2015 እና 16 ዓ/ም በስፋት መተላለፉን በመጥቀስ በ2017 ዓ/ም 8 ለተደራጁ ማህበራትና 16 ፕሎት ለመኖሪያ በመዘጋጀቱ የሊዝ ጨረታ መውጣቱን ተናግረዋል ።

የሌማት ትሩፋት-7ሞዴል አ/አደሮች በደጋማው አካባቢ ከ5-25 ቁጥር ያላቸው የተሻሻሉ ዝሪያ ያላቸው የወተት ላሞች ማርባት ላይ በመሆኑ ወተት በሊትር ከ30-50 ብር እየተሸጠ መሆኑና በማድለብና ማሞከት በትኩረት እተሰራ መሆኑን ጨምረው አንስተዋል ።

በማጂ ከተማ የመብራት ኃይል አቅርቦት ችግር መኖረን ያነሱት አቶ እሸቱ በፌዴራል መንግስት ተጀምሮ የዘገየው በሶላር የሚሰራ የኃይል ማመንጫው በጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ጠይቀዋል ።

የጪዳ ከተማ በ2013 ዓ/ም በከተማ አስተዳዳሪነት የተዋቀረና ብዙ የመልማት አቅምና የማደግ ተስፋ ያለው በመሆኑ ለውጥ ለማምጣት የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የከተማ ካንቲባ አቶ ዓለሙ ኮቾ ገልጸዋል ።

ከተማውን በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር በ6 ሚሊየን ብር 550ሜ የፈሳሽ መውረጃ ዲች፣ በ200ሺ ብር የመንገድ ዳር ዲም ላይት መግባቱ፣ መብራት ባልተዳረሰባቸው 02 ቀበሌ በአንድ ሚሊየን ብር 1410ሜ ከ500 በላይ አባወራን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመብራት ፖል መተከሉ እና በ1.6 ሚለዮን ብር 60 ፖል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ግዥ በመፈጸም ላይ መሆኑ፤ በ4 ሚለየን ብር 4.5 ኪ.ሚ ውስጥ ለውስጥ መንገድ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሠራቱን አንስተዋል።

በኮርደር ልማት የዲዛይንና ወሰን የማከበር ስራን በማስቀደም በዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆኑን ያወሱት አቶ ዓለሙ በመልሶ ማልማት 40 የሚሆኑ ቤቶችንና ሼዶችን ተለዋጭ ቦታና ካሣ በመስጠት በማንሳት የመንገድ ማስፋፊያ የወሰን ማስከበር ስራ መከናወኑ ጨምረው ገልጸዋል።

በሌማት ትሩፋት የስጋና እንቁላል ዶሮ በግል ኢንተርፕራይዝ በመደራጀት ከ1000 በላይ ዶሮ፣ 24 ወጣቶች በ3 ማህበር በመደራጀት ከ1000 በላይ ዶሮ እርባታና የ45 ቀን ጫጬት ማሰራጨት መጀመራቸው ተናግረዋል ።

ሳይፈቀድ የተያያዘ 1415 ውስጥ 1269 ህጋዊ በመሆኑ የማረጋገጫ የሳይት ፕላን መሰጠቱና 146 የፕላን ስምምነት ባለመኖሩ በቀጣይ በዞናል ለውጥ ምላሽ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተሞች ለሰው ልጆች መኖሪያነት ባሻገር የቴክኖሎጂ፣ የአገልግሎት ሰጪና የመንግስት ተቋማት በስፋት የሚገኙበት በመሆናው ለአገልግሎትም ሆነ ለመኖሪያነት ምቹ ለማድረግ፣ ፕላንን ለማስጠበቅ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ከንቲባዎች አንስተዋል።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *