
ራስን በትጥቅ አቅም የመቻል የሪፎርም ስራ ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ሪፎርም ዋነኛ የትኩረት ማዕከል አንዱ በትጥቅ ራስን መቻል እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ጥይት እና ተተኳሽ ከውጭ ሀገራት ትገዛ እንደነበር ያወሱት የግዢ ሂደቱ በሻጭ አካል የተመሰረተ በመሆኑ በሚፈለገው ጊዜ ማግኘት እንደማይቻል ገልጸዋል።
በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በትጥቅ ራስን ለመቻል የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።
የሪፎርሙ አካል በሆነው ሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ አዳዲስ አቅሞች መጨመር እና የዘመኑ ዲጂታል ቁመና ላይ ማድረስ መቻሉን ነው ጠቅላይ ኢታማዦች ሹሙ የገለጹት።
በዚህም ኢንዱስትሪው ለከባድ፣ መከካለኛና ቀላል መሳሪያ የሚሆን ተተኳሽ በሀገር ውስጥ የማመረት አቅም ገንብቶ ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የተገነባው የኢንዱስትሪ አቅም ትውልድ ወይም ገበያን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የተገኘው ስኬት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት አኩሪ የሚባል መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ስራ የሰጡት አቅጣጫ፣ ማበረታቻ እና አመራር ሰጪነት ለተገኘው ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪው አዲስ አመራር ዘመኑ የደረሰበትን የኢንዱስትሪ አቅም እንዲፈጠር የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸውን አመልክተዋል።
በሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የተጀመረው ራስን በትጥቅ አቅም የመቻል እቅድ እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
