ምግብና ሥርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ የብዝሀ ሴክተሮች ቅንጅታዊ አሠራር መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የምግብ ሥርዓት ሽግግር ፍኖተ ካርታ ማስጀመሪያ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ሰብስቤ ሻዎኖ ባደረጉት ንግግር፣ በክልሉ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ካውንስል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ሰብስቤ ሻዎኖ እንደገለጹት፣ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ጉዳይ የአንድ ሴክተር ብቻ ሳይሆን የብዝሀ ሴክተሮች ተቀናጀ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፣ ተቋማት ከምግብ ምርት እስከ መመገብ ድረስ ባለው ሂደት ያላቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የምግብ ዋስትና ሳይረጋገጥ የሥርዓተ ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸው፣ የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር “ምግቤን ከጓሮዬ” እና “ሌማት ትሩፋት” ያሉ ፕሮግራሞችን በተደራጀ መልኩ መተግበር እንደሚገባ ጠቁመው

ይህም ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያግዝም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የምግብ ሥርዓት ሽግግር ክላስተር አራት አስተባባሪ አቶ ደበላ ደበሌ እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ፕሮግራሞች በተቀናጀ እቅድ እየተተገበሩ ነው።

እነዚህ እቅዶች የግብርና ምርትን ማሻሻል፣ የምግብ ጥራትና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የአቅርቦት ስርዓትን ማዋቀር እና ጤናማ እና ተመጣጣኝ ምግብ ለህዝብ እንዲደርስ የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ምግብና ሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ማቲዎስ ማልዳዬ ገለጻ፣ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ከምግብ ምርት እስከ አቅርቦትና አጠቃቀም ያለውን ሙሉ ሂደት በማስተካከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ዘርፉን ለማዘመን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፍኖተ ካርታው ለቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ ይህም ብዝሀ ሴክተሮች የሚያከናዉኑ ተግባራትን በዝርዝር ያካተተ ነውም ብለዋል።

በማስጀመሪያ መድረኩ በክልሉ የምግብ ሥርዓተ አማካሪ ወ/ሮ አቤኮዬ ሽፋራዉ የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ ምግብ ፍኖተ ካርታ ሰነድ እያቀረቡ ይገኛሉ።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *