ሁሉም ባለድርሻ አካላት የክልሉ የታክስ አምባሳደሮች ሊሆኑ ይገባል:- ወ/ሮ ህይወት አሰግድ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ገቢዎች ሚኒስቴርና ጉሙሩክ ኮሚሽን ጅማ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር 4ኛ ዙር የክልል አቀፍ የታክስና ጉምሩክ ክበባት የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር በሚዛን አማን ከተማ እያካኸደ ነው።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ የክልሉን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኝ አስፈላጊውን የፋይናንስ ወረት ከገቢና ታክስ እንዲገኝ ከግንዛቤ ስራ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል።

ቢሮው ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ ገቢ የመሰብሰብ አቅሙን ላለፉት 5 ዓመታት እያሳደገ በተያዘው በጀት ዓመት በ 3 ዕጥፍ ከፍ አድርገው 18.4 ቢልዮን ብር ለመሰብሰብ አቅደው እስካሁን ከ11 ቢልዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በክልሉ ባሉት ሁሉም መዋቅሮች በግንዛቤ የዳበረ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት እውን እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ መጪው ትውልድ በገቢ ላይ የማይናወጥ አቋም ይዞ እንዲያድግ በተማሪዎች ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም ግብር ከፋዩ በታክስ ህጎች ላይ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን በመጥቀስ በትምህርት ቤቶች ላይ የታክስና ጉሙሩክ ክበባት ተቋቁመው በአብቂ መምህራን እየታገዘ የታክስ ሞራሉ ከፍ ወዳለ ደረጃ እያመጣ ይገኛል ብለዋል።

ኮንትሮባንድን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር ዛሬ ላይ የተገኙ ተማሪዎችና ባለድርሻዎች በየ አምባቸው የክልሉ ታክስ አምባሳደር እንዲሆኑ ወ/ሮ ህይወት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በገቢዎች ሚኒስቴር የጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስከያጅ አቶ ነጋሶ አብዲሳ በሀገር አቀፍ ደረጃ ላለፉት ዓመታት በግብርና ታክስ ግንዛቤ ላይ ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የታክስና ጉምሩክ ክበባት ከክበባትነት ያለፈ የሀገሪቱን የመልማት ፍላጎት የሚያሳልጥ መሣሪያ መሆኑን አውስተው በዚህም በሀገር ደረጃ 1.5 ትሪሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በግንዛቤ የበለፀገ ታማኝ ግብር ከፋይ ለማፍራት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የዛሬ ተማሪዎች የነገ ፖሊሲ አመንጪ ስለሆኑ ከወዲሁ የጠራ ግንዛቤ ይዘው ትምህርት በሚያጠናቅቁበት ወቅት ታማኝ ግብር ከፋይ መና አምባሳደር እንዲሆኑና ማህበረሰቡን እንዲያስተምሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ላይ የክልልና ፌደራል የመንገስት የስራ ኃላፊዎች፣ የታክስ አምባሳደሮችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከስድስቱ ዞኖች በተገኙ የክበቡ አባላት ተማሪዎች መካክል የጥያቄና መልስ ውድድር እየተደረገ ይገኛል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *