በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ5 ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ጥቅል ሀገራዊ ምርት በእጥፍ አድጓል – ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ

Spread the love

የዓለም ንግድ ሥርዓት መዛባት ያስከተለውን ጫና የሚቋቋም የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን መከተል በመቻላችን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ5 ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ጥቅል ሀገራዊ ምርት በእጥፍ ማደጉን ነው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የገለጹት፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከአባላቱ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም ላይ እንዳለው ሁሉ በኢትዮጵያም ባለፉት 5 ዓመታት ከፍተኛ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች፣ ኮረና፣ ውጊያ እና የዓለም ንግድ ሥርዓት መዛባት ያስከተለውን ጫና የሚቋቋም የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን መከተል በመቻላችን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ5 ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ጥቅል ሀገራዊ ምርት በእጥፍ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

84 ቢሊየን ዶላር የነበረው ጥቅል ሀገራዊ ምርት በ5 አመት ውስጥ 164 ቢሊየን ዶላር ደርሷል ነው ያሉት፡፡

የዜጎች ነፍስ ወከፍ ገቢያችን 882 ዶላር ከነበረበት 1ሺ 549 ዶላር መድረሱንም እንዲሁ፡፡ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት የአፍሪካ እና የአለም ሀገራት መካከል አንዷ ናትም ብለዋል፡፡

ለሺ አመት በድህነት የነበረችን ሀገር በ10 አመት ልንቀይራት አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነገር ግን ከድህነት ለመውጣት የሚያስችል መሠረት መጣል እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከግብርና አንጻር ብዙ ትኩረት ተሰጥቶ እተሰሠራበት መሆኑን ገልጸው ባለፈው አመት 6 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡ በተለይም የሰብል ምርት 7 ነጥብ 1 አድጓል፡፡ ከ20 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ አርሰን ከ600 ሚሊየን ኩንታል በላይ ሰብስበናልም ብለዋል፡፡

በዚህ አመት ደግሞ ከ22 ሚሊየን ሄክታር በላይ እናርሳለን፤ ከ800 ሚሊየን ኩንታል በላይ እንሰበስባለን ብለን በስፋት እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡

“በበጋ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት የበጋ ስንዴ በመስኖ ለማልማት አቅደናል፡፡ አካሄዳችን እንደሚሳካ ያሳያል” ብለዋል፡፡

በግብርና የጀመርነውን አበረታች ውጤት ማጠናከር አለብን ያሉ ሲሆን ይህንንም የኢትዮጵያ አርሶ አደርና በዘርፉ ያለን አካላት በርብርን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ከኢንዱስትሪ አንጻር 6 ነጥብ 9 በመቶ እድገት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ ዘርፍ ከ12 በመቶ በላይ በመሆን ከፍተኛ እድገት ነው የተመዘገበው፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ 7 ነጥብ 1 በመቶ እና የማኒፋክቸሪንግ ዘርፍም 7 በመቶ እድገት ተመዝግቦበታል፡፡ ያሉን ፋብሪካዎች 47 በመቶ ብቻ ያመርቱ ከነበረበት ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው እንቅስቃሴ አሁን ላይ 55 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡ ይህም ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡

ጨርቃ ጨርቅ 63 በመቶ፣ ቆዳ 58 በመቶ፣ ቴክኖሎጂ 35 በመቶ፣ ኬሚካል 68 በመቶ ደርሷል፡፡ ባሉን ፋብሪካዎች ምርታማነትን መጨመር እንደሚቻል ያሳያል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

“የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታችንን የሚያሳድገው ተኪ ምርት ስለሆነ በፊት ለሀገር ውስጥ 30 በመቶ ብቻ የነበረው ምርት አሁን ላይ 38 በመቶ ሆኗል፡፡ ለአብነትም የከሰል ድንጋይ፣ ከሰል እና የቢራ ገብስ ከውጭ ማስገባት አቁመናል፡፡” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በንግግራቸው፡፡

የአገልግሎት ኢንዱስትሪው 7 ነጥብ 9 በመቶ ነው ያደገው፡፡ ትራንስፖርትና ኮሙኒኬሽን ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡

የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እያደገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *