የኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት የሆነው የዋጋ ግሽበት ዓለም አቀፋዊ ችግር ቢሆንም፤ ይህን ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ገለጸዋል።
እንደ አይ ኤም ኤፍ መረጃ ባለፉት 40 ዓመታት ያልታየ የዋጋ ግሽበት ነው ዓለምን እየፈተናት ያለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው እኛንም እየፈተነን ያለው ብለዋል።
“የኢትዮጵያን ያባባሰው የገቢ አቅማችን ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታ እና የግሽበት እድገት ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ ኑሮ ላይ ጫና አሳድሯል” ነው ያሉት።
የዋጋ ግሽበት የሸቀጥ ወይም የአገልግሎት የዋጋ እድገት ምጣኔ ማለት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኑሮ ውድነት የሚያባብስ አንዱ ምክንያት ተደርጎም ይወሰዳል ብለዋል።
ዘንድሮ ያለው ሁኔታ ሲታይ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጋጋት የሚታይበት እና ይህም እንደሚቀጥል የሚጠበቅ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ የተናገሩት።
የዋጋ ግሽበቱ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 35 በመቶ በዚህ ዓመት ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጸው፤ ይህም በሚቀጥለው ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ያደጉት ሀገራት የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የሚወስዷቸው መፍትሄዎች፣ የኮረና ወረርሽኝ፣ ጦርነቶች እና የዓለም ስርዓት መፈተን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ለማደግ በሚጥሩ ሀገራት ላይ ጫና ማሳደሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
እንዲህ ያለው ፈተና የሚጠበቅ እና የማይቀር በመሆኑ፤ እጅ ያጠራቸው ዜጎች እንዳይጎዱ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ሀብት ለመያዝ ተሞክሯል ብለዋል።
በተልይ በስንዴ፣ በቡና፣ በሩዝ በሻይ ቅጠል ምርታማነትን ማሳደግ፤ እንዲሁም በማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ ስኳር፣ ዘይት ላይ የሚደረግ ድጎማ አቅመ ድካሞችን ከመመገብ፣ ከተማሪዎች ምገባ እና የቤት እድሳት ጋር ተዳምሮ ችግሩን ለመቋቋም ተሞክሯል ብለዋል።
ምርትን በቀጥታ ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው ለማስድረስም፤ በእሁድ ገበያ እና የመሸጫ ማዕከላት በመገንባት ችግሩን ለማቅለል ተሞክሯል ብለዋል።
የቤት ኪራይን በተመለከተ፤ በሕግ መምራት ካልቻልን ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ዜጋ የሚጎዳ በመሆኑ በቅርቡ መፍትሄ ይሰጠዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።
