ችግሮቻችንን በጋራ እኩል የምንገነዘባቸውና የምንረዳቸው ከሆኑ ወደ መፍትሔ መድረስ ይቻላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪ ተናግረዋል፡፡
እየተካሄደ ባለው በ6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሠጡ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በሀገራዊ ችግሮቻችን ላይ የማንግባባ ከሆነ የመፍትሔ አማራጩ ምንም ቢሆን ውጤታማ ለመሆን አስቸጋሪ በመሆኑ ችግሮቻችንን እኩል በመገንዘብና በመረዳት ወደመፍትሔ መድረስ ይቻላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የችግር ትንታኔ ስሜት እንደሚጫነው የገለጹ ሲሆን ስሜት ደግሞ ምክንያታዊ እንዳንሆን እና ከእውነት እንድንርቅ ስለሚያደርግ አያግባባንም ነው ያሉት፡፡
ዋልታ ረገጥና ጽንፈኛ አመለካከቶች በጋራ ተግባብተን ለመፍትሔው እንዳንተጋ ያደርገናልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሁሉም ጫፍ ያሉ ዜጎች በእኩልነት፣ በነጻነት የሚኖሩባት፣ ሁሉም እምነት በእኩል የሚታይበት፣ ሁሉም ቋንቋ እና ባህል የሚከበርበት እና የበለጸገች ሀገር መፍጠር ነው እይታችን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በጋራ መኖርና በጋራ መበልጸግ እንችላለን የሚል እምነት አለን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፡፡
በቅርቡ ከፍተኛ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ሥልጠና በገቡበት ወቅት 2ሺ በማይሞላ ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ 65 ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የብልጽግና ፓርቲን ያህል ሁሉን ያቀፈና አካታች የሆነ ፓርቲ አለመኖሩንም አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮችን ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ ትርክት ነው ሲሉ የገለጹ ሲሆን ነጠላ ትርክት፣ የተዛባና አፍራሽ ትርክት ሀገር አይገነባም ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡
“ታላቅ ትርክት፣ ሀገራዊ ትርክት ይሰበስበናል፤ ከዚያ በተቃራኒ ያለው ይለያየናል” በማለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባለት በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡
