


በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረዉ “የገጠር ተደራሽ መንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና” የተሰኘዉን ፕሮግራም የሚመራዉ ስትሪንግ ኮሚቴ የመጀመሪያ ዙር ዉይይት በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ-ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጇ ሳፒ በዚሁ ወቅት፣ በዚህ ፕሮግራም የክልሉ መንግስት የበጀቱን 30 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ቀሪውን 70 በመቶ የዓለም ባንክ እንደሚሸፍን ተናግረዋል፡፡
የገጠር ቀበሌዎችን ከዋና ዋና መንገዶች ጋር ማስተሳሰር፣ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች የመጠገንና የሚመረቱ ምርቶች ገበያ የሚወጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት የፕሮግራሙ ዓላማ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ፕሮግራሙ በክልሉ ለ5 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በመጀሪያው ዓመት 6 ወረዳዎች ላይ ይተገበራልም ብለዋል፡፡
ከሁሉም ዞኖች የከፋ ችግር ያሉባቸው ወረዳዎች ተመርጠው በጥንቃቄ ወደሥራ እንደሚገባም ነው አቶ ፋጇ የገለጹት፡፡
ይህ ፕሮግራም በክልሉ ያለውን የመንገድና የድልድይ መሠረተ-ልማት ተደራሽነት እጥረትን በተወሰነ መልኩ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
በዚህም በመጀመሪያው ዓመት በአጠቃላይ ከክልሉ መንግስትና ከዓለም ባንክ ከ1 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚመደብ ገልጸዋል፡፡
የቢሮው ም/ኃላፊ እና የዩራፕ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌዲዮን እስጢፋኖስ በበኩላቸው፣ የፕሮግራሙ የ5 ዓመቱን ፕሮጀክት እና የ2017 ዓ/ም ዕቅድ ለስትሪንግ ኮሚቴው ቀርቦ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡
ይህ ፕሮግራም በዋናነት የመንገድ ግንባታ፣ የመንገድ ጥገና፣ ተንጠልጣይ ድልዲይ እና የስትራክቸር ሥራዎችን እንደሚሰራም ነው አቶ ጌዲዮን የተናገሩት፡፡
የፕሮግራሙ መምጣት አስተዋጾው ከፍተኛ ነው ያሉት የቢሮው ም/ኃላፊ፣ በ2017 ዓ/ም ብቻ 66 ኪ/ሜትር የመንገድ ግንባታ፣ 86 ኪ/ሜትር የመንገድ ጥገና እንዲሁም 6 ስትራክቸሮችን ይሰራል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ተግባሩ በክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴ የሚመራ መሆኑን ገልጸው፣ የኮሚቴው አባላት ያነሷቸውን አስተያየቶች ከየዞኖችና ወረዳዎች ጋር በመግባባት ወደ ስራ የሚገባ ስለመሆኑም አስታውቀዋል፡፡
የስትሪንግ ኮሚቴዉ አባላትም ለተግባሩ መሳካት የሚያግዙ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል ሲል ደሬቴድ ቦንጋ ቅርንጫፍ ዘግቧል።
