

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ41 ሺህ ቶን በላይ የቅመማቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በክልሉ ከ90 ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ የቅመማቅመም ምርት እየለማ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሥራት መኩሪያ ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከ56 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን አውስተው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ41 ሺህ ቶን በላይ ማቅረብ መቻሉን እና ከዚህ ውስጥ እርድ፣ ኮረሪማ፣ ዝንጅብልና ቁንዶ በርበሬ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ አብራርተዋል፡፡
በክልሉ የቅመማቅመም ምርታማነትን ለማሳደግና የጥራት ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ከምርምር ተቋማትና ከቡናና ሻይ ቅመማቅመም ባለስልጣን ጋር እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የቅመማቅመም የግብይት ሕግ ያለመኖር ችግር አሁን በመቀረፉ ግብይቱ ወደ ሕጋዊ መስመር እየመጣ መሆኑን ጠቁመው፤ የቅመማቅመም የግብይት ማዕከላትን በየአካባቢው ለማቋቋም ሂደት መጀመሩን አመላክተዋል ሲል ኤፍኤም ሲ ዘግቧል፡፡
