




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት ክልላዊ የመንግሥት እና የፓርቲ ተግባር አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ እየተገመገመ ይገኛል።
በግምገማ መድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በዋና ዋና ዘርፎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በማስፋትና የግብዓት አጠቃቀም በማሻሻል የማሳ ሽፋን ሆነ የምርት መጠን ማሳደግ መቻሉን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም በትምህርትና ጤና የህብረተሰብ የልማት አቅሞችን በማቀናጀት የህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እና ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ በጤናው ዘርፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።
በክልሉ የፀጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው የአርብቶአደር አከባቢዎች በየደረጃው ካለው የፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት በተሰራው ውጤታማ ሥራ በቀጠናው አውንታዊ ሠላምን በማረጋገጥ፥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው።
የፓርቲ መዋቅርም ተግባራት በባለቤትነት በመምራት የመንግሥት ተግባራት ላይ ውጤት እንዲመዘገብ በቁርጠኝነት መምራቱን የገለጹት ዶክተር ነጋሽ የክልሉ እምቅ አቅም ወደ ሀብት ለመቀየር ታስቦ በክልሉ መንግሥት ተዘጋጅተው የወረዳው የመካከለኛ ዘመን አቅድ በተጨባጭ ወደ ተግባር መገባቱንና በዚህም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም እንዲሁ አንስተዋል።
በ2017 ዓ/ም ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ካለፈው ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ውጤት እንዲሁም በተግባር አፈጻጸም ሂደቱም ላይ መነቃቃት የታየበት መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቆሙት።
በመድረኩ የ2017 ዓ/ም የዘጠኝ ወራት የመንግሥት እና የፓርቲ ዝርዝር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ እና የቀጣይ 90 ቀናት የሥራ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጥ የተገለጸ ሲሆን፥መድረኩ የክልሉ የአስፈጻሚ ተቋማት የሥራ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዞንና የወረዳ እንዲሁም የከተማ አስተዳደር የፊት አመራሮች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
