
xxxxxxxxxxxxxxxxx
በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና ጽዱ ለማድረግ አስፈላጊ የከተማ መሠረተ ልማት አውታሮችን ከመዘርጋት በተጨማሪ ሀገራዊ ኢንሼቲብ የሆነው ጽዱ ኢትዮጵያ እና ኮሪደር ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጽዱ ኢትዮጵያና የኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ፣ በህገወጥ መንገድ የተያዙ የከተማ መሬቶችን ህጋዊ ማድረግ፣ የከተማ መሬት አቅርቦትና ዝግጅት እንዲሁም የከተማ ፕላን ዝግጅት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ከተሞች ለነዋሪዎች ለኑሮ ምቹና ፅዱ የሚሆነው እንዲሁም አንድን ከተማን ከተማ የሚያስብለው አስፈላጊ የከተማ መሠረተ ልማቶች ሲሟሉ ሲሆን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተጀመረው ጽዱ ኢትዮጽያ እና ኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ ለከተሞች መሠረተ ልማት ፣ለከተሞች ውቤትና ገጽታ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል።
በዛሬው ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳ! ዝግጅታችን አጠቃላይ የከተማ ልማት ሥራዎችን በሚመለከት የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
”ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳ ዝግጅት”ከቢሮ ኃላፊው ጋር የተደረገው አጠቃላይ ዝግጅት እንደሚከተለው ቀርበዋል መልካም ንባብ!
👎መ/ኮ ፦ በቅድሚያ ለቃለ ምልልሱ ፍቃደኛ ስለሆኑ እያመሰገንን፤ እንተዋወቅ ስምና ኃላፊነትዎን ቢገልጹልን?
👉እንግዳችን፦ እኔም አመሰግናለሁ ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ! ስሜ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ

👎መንግሥት ኮሙኒኬሽን ፦በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና ጽዱ ለማድረግ እንዴት እየተሰራ ይገኛል?
👉ኢንጂነር የማታለም ቸኮል፦በክልሉ ብዝሃ ዋና ዋና ከተሞችና ተደራሽ ከተሞችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ታዳጊና ማዘጋጃ ከተሞች ይገኛሉ። እነዚህን ከተሞችን ለነዋሪዎች ጽዱ ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ሳቢ ለማድረግ በመንግሥት እና በህብረተሰብ ተሳትፎ ሰፊ ሥራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ ።
ከተሞችን ጽዱና ምቹ በማድረግ ረገድ በክልል ደረጃ የከተማ ጽዳት ደንብ ተዘጋጅቶ በመስተዳድሩ ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ነው ኃላፊው ያስረዱት።
ከዚሁ መነሻ የከተማው ነዋሪዎችም በየአስራ አምስት ቀን ከተሞችን ከማጽዳት ባሻገር በቋሚነት በከተሞች የጽዳት ሠራተኛ ቀጥሮ ዋና ዋና ጎዳናዎችን እንዲያጸዱ ማድረግና ነዋሪዎች እና የመንግስት ተቋማት አከባቢውን ማጽዳትና ለሥራ ምቹ አከባቢ ከመፍጠር አኳያ የሚታዩ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው።
ቢሆንም በከተሞች በቂ የቆሻሻ ማንሻ ቁሳቁስ፣ ቆሻሻ መድፊያ ቦታ፣ ቆሻሻ ማመላለሻ መኪና እና ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ጉዳይ አሁንም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ የሚገባዉ ነው።
👎መ/ኮ፦ በክልሉ የኮሪደር ልማት ሥራን እንዴት ይገልፃሉ፣በስንት ከተሞች ነው ሥራው የተጀመረው፣አፈጻጸሙ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
👉ኢንጂነር የማታለም ቸኮል፦ የኮሪደር ልማት ሥራ በክልሉ ቀድሞ በተመረጡ በሚዛን እና ቦንጋ ከተሞች ሥራው ተጀምሮ እየተተገበረ ይገኛል።
በዚህም ቦንጋ ከተማ ቀድሞ ከተማን መልሶ ከማልማት አንጻር ካፋ ቡና ብሄራዊ ሙዚየም አካባቢ ያሉ ቦታዎችን መልሶ ማልማትና ዙሪያውን ከማጠር አንጻር ከቦንጋ ዩንቨርስቲ ጋር የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ናቸው።
በኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ በቦንጋ ከተማ በአንደኛው ዙር 0.9 ኪ/ሜ ማልማት ተችሏል። በዚህም የእግረኛ መንገድ፣ አረንጓዴ ቦታዎች ማልማት፣ መዝናኛ ቦታዎች እንዲሁም የከተማን ውበት የሚያበላሹ ከፕላን ውጪ የተገነቡ ሼዶችና ኮንቴነር በማንሳት ከተማውን የማልማት ሥራ ተሠርቷል።
በቦንጋ ከተማ በሁለተኛው ዙር ከ5-6 ኪ/ሜ የሚደርስ ደረጃውን የጠበቀ ኮሪደር ልማት ለመስራት የዲዛይን ስራ ተጠናቆ በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል።
በሚዛን አማን ከተማ ኮሪደር ልማት 23 ኪ/ሜ የከተማውን ውበት የሚያበላሹ ሼዶች ማንሳት እና አንድ ኪ/ሜ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ አቀማመጥ ጋር የሚስማማ ዲዛይን ተሰርቶ ወደ ሥራ በመግባት አፈጻጸሙ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የኮሪደር ልማት ሥራ ጥራቱና ደረጃውን ጠብቆ በተያዘው ጊዜ የሚጠናቀቅ ባህር ያለው ፕሮጀክት ነው።
ቀጣይ በሚዛን እና ቦንጋ ከተሞች ቀሪ ሥራዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፈጸም ባለው አቅምና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሚሰራ ይሆናልም።
በክልሉ ከቦንጋ እና ሚዛን አማን ከተማ በተጨማሪም በዋቻ ከተማ ፣ ሺሺንዳ እና ታርጫ ከተማ የመሃል መንገድ፣ ገሳ ከተማ፣ ዳካ ከተማና በሌሎች ከተሞች ሥራው ተጀምሮ መነቃቃቶች እየታዩ ነዉ።
በዋናነትም በኮሪደር ልማቱ በዋና ዋና መንገዶች ሳይሰራ የቆዩ ለአብነት ከጎጀብ እስከ ቦንጋ መንገድ ማጽዳት፣ የፕላን ጥሰት ያለባቸው ግንባታዎች ማንሳትና የማሳመር ሥራ ተጀምሯል።
በዚህም በክልሉ ትላልቅ ከተሞች፣ በዞኑ የሚገኙ ከተሞችና ማዘጋጃ ከተሞች ዋና ዋና መንገዶች ላይ ኮሪደር ልማት ለመስራት በንቅናቄ ሥራዎች እየተከናወኑ ነዉ።
ሀገራዊ ኢንሼቲቭ የሆነው የኮሪደር ልማትን በክልሉ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ ስራው እንዲከናወን አቅጣጫ ተቀምጧል።በቅርብ ጊዜ በሁሉም ከተሞች የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ ይሰራል።
👎መ/ኮ ሳይፈቀድ በህገወጥ መንገድ የተያዙ የከተማ መሬቶችን ህጋዊ ከማድረግ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?
👉ኢንጂነር የማታለም ቾኮል ፦ቀደም ሲል በክልሉ ባሉት ከተሞች 32 ሺህ ሳይፈቀዱ የተያዙ የከተማ መሬቶች ነበሩ።

ከዚህም እስካሁን 29 ሺህ ቁራሽ መሬቶችን ልኬት፣ ለ24 ሺህ ሳይት ፕላን ማዘጋጀት እንዲሁም 19 ሺህ የሳይት ፕላን በመስጠት ግለሰቦች የመሬት ባለቤት የማድረግ ሥራ ተሰርቶ በዚህም 201 ሚሊዮን ብር ገቢ ክልሉ ማግኘት ችሏል።
ግለሰቦች ሳያስፈቅዱ የከተማ መሬትን መያዝ መሬቶችን ለህገወጥነትና ለፕላን ጥሰት የተጋለጠ ከማድረግ ባለፈ መንግስት ከከተሞች ሊያገኝ የሚችለውን ግብር እንዳያገኝ እና ከተሞች ከሚያመነጩት ሀብት የመሠረተ ልማት ጥያቄዎቻቸው እንዳይመለስ የሚያደርግ በመሆኑ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ቀጣይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላሉ።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት ሳይፈቀድ የተያዘ የከተማ መሬትን ለመቆጣጠር ለመከላከል ደንብ ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን ደንቡም ህገወጥነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ፣ የከተማ ፕላን ለማስጠበቅና መንግስት ከከተሞች ሊያገኝ የሚችለው ገቢ እንዲያገኝ ይረዳል።
👉መ/ኮ ፦ የከተማ መሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በክልሉ የከተማ መሬቶችን በሊዝ ሆነ በጨረታ መልክ ለግለሰቦችና ለማህበራት ከማስተላለፍ አንጻር ምን እየተሰራ ነው?
👎ኢንጂነር የማታለም ቾኮል፦በየዓመቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች መሬት እንደሚዘጋጅም ያነሱት ኃላፊው በዘንድሮ ግማሽ ዓመቱ 446 ሄክታር መሬት ለማዘጋጀት ታቅደው 377 ሄክታር መሬት ለተለያዩ አገልግሎቶች ተዘጋጅቷል።
እነዚህም በዋናነትም ለማህበር ቤት ግንባታ፣ ለግለሰቦች፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለመንግሥት ተቋማት፣ኢንተርፕራይዝ እንዲሁም ለልማት ተነሺዎች ካሳ የሚዘጋጅ መሬት ነው።
በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ከተዘጋጀው መሬት 324 ሄክታር ለማስተላለፍ ከታቀደው እስካሁን 284.6 ሄክታር ለተለያዩ አገልግሎት ማስተላለፍ ተችሏል።
መሬት በሁለት መልኩ የሚተላለፍ እንደሆነም ያነሱት ኃላፊው አንደኛ በምደባ ፦እነዚህም ለማህበር ቤት ግንባታ፣ ለመንግሥታዊ ተቋማት፣ ለትላልቅ ኢንቨስትመንት ሲሆን በግማሽ ዓመቱ በምደባ 240 ሄክታር ለማስተላለፍ ታቅደው 169.7 ተላልፏል።
ሁለተኛው በሊዝ መልክ የሚተላለፍ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት 80 ሄክታር መሬት ለማስተላለፍ ታቅዶ 114 በማስተላለፍ ከእቅዱ በላይ የተሳካ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ በመሬት ዝግጅት እና ትልልፍ የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
የማህበራት መሬት ዝግጅትና ትልልፍ ጋር አያይዞም ሀሳብ ያነሱት ኢንጂነር የማታለም ቸኮል የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ክልሉ ከተደራጀ ከ2014 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ በከተማ ነዋሪዎች ለመኖሪያ ቤት ለ256 ማህበራት፣ በመምህራን 316 ማህበራት፣ በክብር ለተሰናበቱት የመከላከያ ሠራዊት 148 ማህበራት አጠቃላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ710 ማህበራት ከተደራጁት ውስጥ 503 ማህበራት 107.126 ሄክታር መሬት ተላልፏል።
በተያዘው በ2017 በ1ኛው ግማሽ ዓመት የከተማ ነዋሪ ለ11ማህበራት ፣ በመምህራን 26 ማህበራት እንዲሁም በክብር ለተሰናበቱ ለመከላከያ ሠራዊት 16 ማህበራት ባጠቃላይ 53 ማህበራት ከተደራጁት ውስጥ መሬት ያገኙ 16 የነዋሪ ማህበራት፣ 14 የመምህራን ማህበራትና 15 የክብር ተሰናባች መከላከያ ሠራዊት በድምሩ 45 ማህበራት 9.27 ሄክታር መሬት ተዘጋጅተው ተላልፏል።
ይህም በዋናነት በሊዝ ተወዳዳሪው መሬት ማግኘት የማይችሉ የመንግስት ሰራተኞች፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም በክብር የተሰናበቱ የመከላከያ ሠራዊት በአነስተኛ ቁጠባ በማህበር ተደራጅተው መሬት እንዲወሰዱ የሚደረግ ነው።
ቀሪ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በማህበር ተደራጅተው መሬት ላላገኙ ማህበራት በከተሞች መሬት በማዘጋጀት ማህበራት መጠናከራቸው እና ቁጣባ ማጠናቀቃቸውን በማረጋገጥ መሬት የማስተላለፍ ሥርዓት በመዘርጋት ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ይሰራል።
👉መንግሥት ኮሙኒኬሽን :-በክልሉ ከተሞች አስፈላጊ የከተማ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ምን እየተከናወነ ነው የተመዘገቡ ውጤቶችስ ?
👎 ኢንጂነር የማታለም ቸኮል ፦በክልሉ ባሉት ከተሞች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ለመዘርጋት በመንግሥት ሆነ በህዝብ ዘንድ ያለው መነሳሳት ከፍተኛ ነው።
ለከተሞች ልማት በዘንድሮ ዓመት በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት በጊዜው ወደ ታች ባይወርድም 17 ሚሊዮን ገንዘብ ማቺኒግ ፈንድ ተመድቧል።
በግማሽ ዓመቱ በከተሞች በመንግሥት ሆነ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተሰሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሚመለከት 96 ኪ/ሜ አዲስ መንገድ ከፈታ ለማከናወን ታቅደው 87 ኪ/ሜ አዲስ መንገድ ውስጥ ለውስጥ ከፈታ፣ ጠጠር ማልበስ 43.2 ኪ/ሜ ታቅደው 35.1 ኪ/ሜ ጠጠር የማልበስ ሥራ ተሠርቷል።
በየዓመቱ ከተማ አስተዳደሮች ማዘጋጃ ቤቶችና ህብረተሰቡ ለመንገድ ልማት ሥራ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ባለፉት ግማሽ ዓመት 24 ኪ/ሜ የመንገድ ዳር መብራት ለመዘርጋት ታቅደው 17.2 ኪ/ሜ ዝርጋታ ተከናውኗል።
የውሃ መስመር ዝርጋት በየከተሞች መሰራቱን የጠቆሙ ሲሆን በዚህም 15.5 ኪ/ሜ የውሃ መስመር ዝርጋታና ሶስት የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ቦታዎች የማጽዳጃ ቤት መገንባት ተችሏል ።
የህብረተሰብ ተሳትፎ በመሠረተ ልማት በግማሽ ዓመቱ ከ32 ሚሊዮን በላይ ብር ፣ የጉልበት ተሳትፎ በገንዘብ ሲተመን 17.9 ሚሊዮን እንዲሁም በቁሳቁስ ድጋፍ 9 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል።
በግማሽ ዓመቱ ከማዘጋጃ ቤቶች 517 ሚሊዮን ብር ለከተማ መሰረተ ልማት ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ከተሞች ያላቸውን አቅም አሟጦ በመጠቀም ገቢን በመሰብሰብ ለከተማ መሠረተ ልማት ማዋል ይገባቸዋል።
👉መንግሥት ኮሙኒኬሽን፦ በክልሉ የፕላን ዝግጅት ሥራ እንዴት እየተሰራ ነው የእስካሁን አፈጻጸም ምን ይመስላል?

👎ኢንጂነር የማታለም ቸኮል የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው ከተሞች በፕላን መመራት አለባቸው። በክልሉ አጠቃላይ 112 ከተሞች እንዳሉትም ያነሱት ኃላፊው ሚዛን እና ቦንጋ ከፈርጅ ሁለት ወደ አንድ የተቀየሩ ናቸው ።ታርጫ እና ቴፒ ወደ ፈርጅ ሁለት ያደጉ ሲሆን ሌሎች 16 ከተሞች ፈርጅ ሶስት ፣ 24 ከተሞች ፈርጅ አራት እና 67 ከተሞች ፈርጅ አምስት ደረጃ ያሉ ከተሞች ናቸዉ።
በክልላችን ፕላን የሌላቸውን ከተሞች እንደለሉት ያስታወቁት ኢንጂነር የማታለም ቸኮል ከተሞቻችን ልዩ የሚያደርገው ሁሉም ከተሞች ወደ ከተማ ደረጃ ሲያድጉ በፕላን መሠረት ሲሆን በክልሉ የሚገኙ 112 ከተሞች ፕላን ያላቸው ናቸው።
በግማሽ ዓመቱ በአምስት ከተሞች መሠረታዊ ፕላን ለመስራት ታቅደው በአራት ከተሞች የተሰራ ሲሆን እነዚህም ከጪ፣ ፋጀቃ ግዕዝ መሬትና ኮባጂ ከተሞች ናቸው ።
ገጠር ላይ ወደ ከተማ ደረጃ ያላደጉ የገጠር ስኬች ፕላን ማዕከላት እንዳሉትም አንስተው በእነዚህም 7 ፕላን ለማዘጋጀት ታቅደው ስድስት ማዘጋጀት ተችሏል።
ሌላው ከተሞች አስተዳደር ወሰን ከማካለል አንጻር በሁለት ከተሞች አስተዳደር ወሰን ለማካለል አቅደን ሶስት መስራት ተችሏል።
ከተሞች ስትራክቸር ፕላን የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በተለይም ቴፒ ከተማ ቀድሞ የተሰራዉ የፕላን ዝግጅት ችግር ያለበት በመሆኑ ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎችና ከፌደራል ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቴፒ ስትራክቸር ፕላን እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸው ቦንጋም ስትራክቸር ፕላን አስፈላጊ በመሆኑ ቀጣይ ለመስራት ዕቅድ ተይዟል።
ከፕላን ዝግጅት አንጻር ያለን የሰው ኃይልና ውስን ሀብት በመጠቀም የተሰሩ ሥራዎች ከእቅዱ አንጻር የተሻለ ነዉ።
ቢሆንም ካለው ፍላጎት አኳያ ቀጣይ አቅማችንን በሰው ኃይል፣በበጀትና ቁሳቁስ በማደራጀት ፕላን ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ የፕላን ችግር ያለባቸውን መከለስና ማስተካከል እንዲሁም NDP በማዘጋጀት የደቀቁና የቆዩ ብሎም የፕላን ማስጠበቅ ችግር ያለባቸውን መልሶ የማልማት ሥራ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል።
ከተሞቻችን ለቀጣይ ትውልድ ምቹ እንዲሆን የአሁኑ ትውልድ ከሌሎች ከተሞች ልምድ በመውሰድ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበትና ህብረተሰቡ እስካሁን ለከተማ ልማት እያደረጉ ያሉ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን አጠናክረው ማስቀጠል አለባቸዉ ።
በከተሞች የሚሰሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በፍትሃዊነት ተደራሽ ማድረግ፣ የሚሰበሰበው ሀብት በአግባቡ አገልግሎት ላይ በማዋል ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ውስን የከተማ መሬት በአግባቡ መዝግቦ መያዝና ማስተዳደርና ላይ ቢሮው በትኩረት የሚሰራዉ ተግባር ነዉ።
