



በቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ለተለያዩ አገልግሎት እንዲውል ታስቦ በ7.7 ሚሊዮን ብር ወጭ እየተሰራ የሚገኘው የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መጠናቀቁ ተገልጿል።
የኮሌጁን የንጹህ መጠጥ ውሃ ቁፋሮና ግንባታ ሥራን የደቡብ ምዕራብ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በውል ተረክበው እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎች የሥራ አፈጻጸም ሂደት ያለበትን ደረጃ በቦታው ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።
በምልከታ ወቅት የደቡብ ምዕራብ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማኑኤል አሰፋ ኮርፖሬሽኑ በ2016 ዓ.ም ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ ትርፋማነቱን እና ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የንጹህ መጠጥ ግንባታ፣ የህንጻ ግንባታ፣ የመስኖ ግንባታና ሌሎች መሠል ኮንስትራክሽን ነክ ሥራዎችን ከመንግስት እና ከግል ተቋማት በውል ተረክበው በጥራትና በፍጥነት እየሰራ ስለመሆኑን ገልጸዉ የቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ግንባታ የዚሁ አካል ነውም ብለዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነዉ የደቡብ ምዕራብ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች በርካታ ኮንስትራክሽን ነክ ግንባታ ሥራዎችን በጨረታና በድርድር በመረከብ እየሰራ እንደሚገኝ ያብራሩት ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር ተዘራ ሽጉጤ ናቸዉ።
ኮርፖረሽኑ ተረክበዉ ከሚሰራቸው መካከል የቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ አንዱ ነው ያሉት ኢንጂነር ተዘራ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ቁፋሮ በተያዘለት ጊዜና ውል መሠረት በጥራትና ፍጥነት መጠናቀቁንም አብራርተዋል።
በቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርና የኮሌጁ ዋና ዲን ዶ/ር) ዲባሌ ሣህሌ በበኩላቸው ኮሌጁ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር ሥራዎች እና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ኮሌጁ ለሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አገልግሎት መስጠት እንዲችል በ7.7 ሚሊዮን ብር ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ቁፋሮና ግንባታ እያሰራ መሆኑንም ተናግረዋል የኮሌጁ ዋና ዲን ዶ/ር ዱባሌ ሣህሌ።
ውሃዉ በኮሌጁ ውስጥ ለሚከናወኑ ላብራቶሪ አገልግሎት፣ የአትክልት ልማት፣ ለተማሪዎች ንጽህና፣ ከብት እርባታ ሌሎች ሥራዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እየተሰራ የሚገኝ መሆኑና ቀጣይ የውሃ አቅርቦት መጠኑ እየታዬ ከኮሌጁ ባሻገር ለአከባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋልም ብለዋል።
በፍቅር ከበደ
