ብልፅግና ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ከመቼውም በላይ ተቀራርቦ እየሰራ ነው – አቶ መለሰ ዓለሙ::

Spread the love

ብልፅግና ፓርቲ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን በብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ተናገሩ።

ፓርቲው ይህን የሚያደርገው ዴሞክራሲ እንዲዳብርና በሀገር ጉዳይ ተቀራርቦ የመስራት ባህል እንዲጎለብት በማሰብ መሆኑን አቶ መለሰ ገልጸዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

አቶ መለሰ በመድረኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ ፓርቲው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን በመያዝ ለህዝብ ቃል የገባቸውን የልማት ስራዎች በመፈጸም ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም ሀገር ከማሻገር ጎን ለጎን በተለያዩ መስኮች ውጤታማ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞን ቀጣይና ዘላቂ ለማድረግ በዴሞክራሲ መስክም ስልጣን በህዝብ ፈቃድ ብቻ የሚስተናገድባት ሀገር ለመገንባት ፓርቲው ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት።

የዴሞክራሲ እሴትና የፖለቲካ ባህል ለውጥ የሚመጣው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በፉክክርና በትብብር ማዕቀፍ አብሮ የመስራት ባህል ሲያድግ ነው ብለዋል አቶ መለሰ ።

ሲቪል ማህበራትም ዴሞክራሲን የሚሸከም ባህል ለመገንባት በትብብርና በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ባለፉት 9 ወራትም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁሉም ክልሎች ተደራጅተው በጋራ እንዲሰሩ፣ ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ፤ ሲቪል ማህበራትም ከዲሞክራሲ ልምምድ ባሻገር በልማቱ ውስጥ ያላቸው አበርክቶ እንዲያድግ ተሰርቷል ብለዋል።

የተረጋጋ ሀገር ለመገንባት ስልጣንን በኃይል ለመያዝ ከመሞከር አስተሳሰብ የተላቀቀ ትውልድ እንዲፈጠርም ብልፅግና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሰፊ ምክክር እያደረገ መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ግርማ መለሰ በበኩላቸው፥ ሀገራዊ ለውጡ ኢ-ፍትሐዊነትና ፅንፈኝነት ስር እንዳይሰዱ በማክሸፍ ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ መሰረት መጣሉን አንስተዋል።

በክልሉ ለውጡን ለመቀልበስ አንዳንድ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ ህዝብን በማስተባበር ፅንፈኝነትን የማስወገድና የአስተሳሰብ ለውጥ የማምጣት ስራ ተሰርቷል ብለዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *