
የክልሉ ፐብልክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ብቃት ያለው የተቋማት የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስራዎችና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች፣የሰው ሀብት ስራ አመራር ስርዓት፣የመንግስት አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት የማስፈንና የፀረ-ክራይ ሰብሳቢነት ትግል የማጠናከር እና አገራዊ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራትን ከማዘመን አኳያ ልዩ ትኩረት ሰጥተዉ ኃላፈነቱን እየተወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዚህ መሠረት የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናና ውጤታማ ለማድረግ በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዋና ዋና እቅዶች ትግበራን መሠረት በማድረግ ከቢሮዉ ሃላፊ አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡መልካም ንባብ!
የመ/ኮ– በመጀመሪያ መረጃ ለመስጠት ከእኛ ጋር ለመቆት ፍቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ – እኔም አመሰግናለሁ!
የመ/ኮ- ወደ መጀመሪያ ጥያቄ ስናመራ፡-የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናና ውጤታማነትን ለማሳደግ እንዴት እየተሰራ ይገኛል?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ– ቢሮዉ በበጀት አመቱ ብቃት ያለው የተቋማት፣የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስራዎችና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች፣የሰው ሀብት ስራ አመራር ስርዓት፣የመንግስት አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት የማስፈንና የፀረ-ክራይ ሰብሳቢነት ትግል የማጠናከር እና አገራዊ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራትን ከማዘመንና የሪፎርም ሥራዎችን ትኩረት በመስጠት እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
የመ/ኮ- የሪፎርም ሥራዎችን ተቋማዊ መሰረት ከማስዝ አንጸር ያለዉ ሂደትስ?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ -የሪፎርም ሥራዎችን ተቋማዊ መሰረት ለመጣልና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመስራትና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ከሰዉ አጅ ንክክ ነጻ በሆነ መንገድ አንዲሰጥ ለማስቻል የጠቅላይ ሚኒስትራችን ኢኒሼቲቪ የሆነዉን የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አንደ ክልል በሚዛን አማን ከተማ ግንባታ በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የዜጋ ተኮር አገልግሎት አሰጣጥ ያለውን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ዜጎቹን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል የአሰራር ቅልጥፍናን እና ተጠያቂነትን በማሻሻል በኩል አመርቂ ዉጤት እያተመዘገበ ይገኛል፡፡ለአብነትም፡-በሚዛን አማን የመሶብ አንድ ማዕከል ዉስጥ 5 የክልል ተቋማት እና 4 የፌዴራል ተቋማት በድምሩ 9 ተቋማት 35 የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
መ/ኮ–ማዕከሉ ስራ ከጀመረበት እስከሁን ድረስ ለምን ያህል ዜጎች አገልግሎት ተደራሽ አድርጓል?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ -ማዕከሉ ስራ ከጀመረበት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረ ድረስ 10ሺህ386 ተገልጋዮች በአካል የተስተናገዱ ሲሆን 1ሺህ805 ተገልጋዮች ደግሞ በon line አገልግሎት ለማግኘት ችለዋል፡፡ ይህም በተለያዩ መንገዶች ሊከሰት የሚችለዉን የዜጎችን መጉላላት በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ነዉ፡፡ የመንግስት አገልግሎቱን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ አንደ ሀገር በተያዝዉ አቅጣጫ መሰረት በ 5 ከተማ አስተዳደር የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስፋፋት ከዞኖችና ከከተማ አስተዳደር ለተዉጣጡ አመራርና ባለሙያዎች የተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት ወደ ተግባር እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን ወደ መሶብ አንድ ማዕከል ተግባር ለመግባት የህንፃ እና የአገልግሎት ልየታ ስራ እየተሰራ ነዉ። በተጨማሪም በ15 ከተማ አስተዳደሮች ተጨማሪ የመሶብ አንድ ማዕከል ለማስፋፋት የዝግጅት ምዕራፍ በመከናወን ላይ ነዉ፡፡
መ/ኮ-የሪፎርም ሥራዎች ትግበራን ከማጠናከር አኳያ ቢሮዉ ተግባሩን እንዴት እየተወጣ ይገኛል?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ – በመንግስት አገልግሎትና አስተዳር ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ትግበራ ሰነድ፣የፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች እና የፍኖቴ ካርታ ክልላዊ ይዘት ጠብቆ የማዘጋጀት ስራ ተሰርቷል። በክልላችን በመጀመሪያ ዙር ወደ ሪፎርም የሚገቡ ተቋማት ጤና፤ክህሎት እና ፋይናንስ ቢሮ ሲሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዲያጠናቅቁ በመደረግ ላይ ነዉ፡፡ ከተለዩ ተቋማት ዉስጥ ለጤና ቢሮ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ለስራና ክህሎት እና ለፋይናንስ ቢሮ ስልጠናዉን ለመስጠት ፕሮግራም ተይዟል፡፡ በተጨማሪም ከቦንጋ ዩኒቭርሲቲ ጋር በሪፎርም ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መግባቢያ ሰነድ በማዘጋጀት የማቅረብ ስራ የተሰራ ሲሆን ዉሳኔያቸዉን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡
በገጠር ቀበሌ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናና ዉጤታማነት ለማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጡን አደረጃጀትና አሠራር ለማሻሻል የአቅም ግንባት ስልጠና ለቀበሌ ስራ አስኪያጆች ለመስጠት በታቀደዉ መሠረት በሁሉም ቀበሌ ተደራሽ ለማድረግ የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት በዞኖችና በወረዳዎች ስልጠናዉ ተደራሽ የማድረግ ስራ አየተሰራ ይገኛል፡፡
የመ/ኮ-የአፈጻጸም ሥራ አመራር ሥርዓት ውጤታማነትን ማጠናከር አስፈላጊነት በመረዳት መትጋት ተገቢ በመሆኑ እንዴት እየተከደበት ይገኛል?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ – በክልል፣በዞን እና በወረዳዎች በሚገኙ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች ያሉበትን ደረጃ ምልከታ ለማድረግ የተደራጀ ቼክ ሊስት በማዘጋጀት 2 ዙር በ96 ተቋማት ላይ በአካል በመገኘት ድጋፋዊ ክትትል የማድረግ ሥራ ተሰርቷል።
የመ/ኮ-የመልካም አስተዳደር መርሆች ትግበራን ከማጠናከርን አኳያ ጅምር ተግባራት በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ – በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ የውስጥና የውጭ መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በክልሉ መንግስትና ብልጽግና ፓርቲ በተሰጠዉ ትኩረት ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እቅድ በሁሉም ተቋማት እንዲዘጋጅ በማድረግና በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ልዩ ትኩረት የሚሹ ተቋማት በመለየት ዉይይቶችንና ግምገማዎችን በማካሄድ በተግባር ሂደት የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲታረሙ በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ወደ ትግበራ በመግባት ማስተካከያ ተወስዷል፡፡ የመልካም አስተዳደር መርሆች ማስተግበሪያ ማኑዋል በመከለስ የተዘጋጀ ሲሆን መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ሥልጠና በክልል ለ130 እና በዞኖች 1587 ተሳታፊዎች ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ 2157 የዉስጥና የዉጪ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተለይቶ የታቀደ ሲሆን 1600 (74%) መፍታት ተችሏል፡፡ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ ክሶች መቀነስ ችለዋል፡፡
የመ/ኮ-በሰዉ ሃብት አመራር ልማት ዘርፉን ከመገንባት እና ከማብቃት አኳያ ያሉ እንቅስቃሴዎች ላይ ያሉ አፈጻጸሞችን ብገልጹልን?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ – የሰራተኞች ክልላዊ የሥራ መደብ ለማሻሻል 3873 (57%) መታወቂያ ቁጥር ተሻሽሏል።የእንስፐክሽንና የሰዉ ሀብት ህጎች ማሻሻያ ስርዓት ከመገንባት አንጻር፤በሰዉ ሀብት ስራ አመራር ስርዓቶች አፈጻጻም 170 ከሚመለከታቸዉ አካላት ምክክር ተደርጓል። የመንግሥት መ/ቤቶች በሚፈፀሙ የሰው ኃይል ስምሪት (ቅጥር፣ዝውውር፣ደረጃ ዕድገትና ምደባ) 5850 የሠራኞችን ፋይል የምርመራ ስራ በማከናወን ሊባክን የነበረ 668ሺህ500 ብር የመንግስትና የህዝብ ሃብት ለማዳን ተችሏል።
የመ/ኮ-የመጨረሻ ጥያቄያችን የምናደርገዉ ቢሮዉ የሰዉ ሀብት ልማትና ጥናት ዘርፍ ለማጠናከር ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?
አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ – የስልጠና ፍላጎት በመለየት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለመጀመሪያ ድግሪ ምልመላ በማካሄድና የመግቢያ ፈተና እንድወስዱ በማድረግ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም እንዲከታተሉ ተደርጓል። የመንግስት ሰራተኞች መረጃ ቆጠራ በዲጂታል የመመዝገብ ስራ /ICSMIS/ ለማካናወን እንደሀገር የተጀመረ ሲሆን በክልላችን የቅድመ ዝግጅት ስራ በማከናወን ላይ እንገኛለን። የመንግስት ሰራተኞች መረጃን በዘመናዊ ተክኖሎጂ ተጠቅመን ለማደራጀት የICSMIS ስራ ለማቀላጠፍ ከክልላችን ኢኖቬሽንና ተክኖሎጂ ቢሮ፣ ከፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽንና ከኢኖቬሽንና ተክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የወረዳ ኔት ዝርጋታ ተከናዉኗል። የመንግስት ሰራተኞች መረጃ ምዝገባ ስራ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዉ የክልል ተቋማት ምዝገባ ተጠናቅቆ የስራ ሂደቶችና የስራ መዝርዝር ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን በፌደራል ስቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በተቀመጠዉ ጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በክልላችን ዉስጥ የሚገኙ 6 ዞኖች፣41 ወረዳዎች፣20 ከተማ አስተዳደሮች፣839 የገጠር ቀበሌዎች 93 የከተማ ቀበሌዎች ተለይቶ ወደ ICSMIS ምዝገባ ዝግጁ ሆኗል። የሰራተኞች ቆጠራ የሚካሄድባቸዉን ቦታዎች የመለየትና ቆጠራዉን የሚያካሄዱ ባለሙያዎችን የመመልመል ስራ ተከናዉኗል።
በአስተዳደር ፍርድ ቤት ጠቅላላ የቀረበዉ የይግባኝ መዝገብ 32 ስሆን ዉሳኔ የተሰጠ 32 (100%) ሲሆን የቀረቡ የይግባኝ ሥራ ክርክር መዝገቦች ላይ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 29/2016 አንቀጽ 80/3/ መሠረት ተግባራዊ ማድረግ ተችላል።
ሆኖም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ወደ ዲጂታል አገልግሎት የማስገባት የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጮችን በመለየት የመከላከል ስራዎችን የማጠናከርና የሚቀርቡ አቤቱታዎችንና ቅሬታዎችን ፈጣን ምላሽ የመስጠት የሰራተኞችን ቆጠራ በወቅቱና በጥራት ማጠናቀቅ እና በሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶች የተገልጋዩን እርካታ የማሳደግ ስራ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡አመሰግናለሁ!
የመ/ኮ– እኛም ስለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን!
በካሳሁን አሰፋ
