ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ፍትህን ለሁሉም ከማድረስ ባሻገር ለመደበኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የስራ ጫናን እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

የእርቅ ተኮር ፍትህ እና የባህል ፍርድ ቤቶች ስራዎችን ለመገምገም ጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ወደ ስራ በገቡበት አካባቢ በፍትህ ተደራሽነት ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

የለውጡ መንግስት ከሚተገብራቸው ሪፎርሞች አንዱ የፍትህ ሪፎርም ስራ በመሆኑ ለስኬቱም የባህላዊ ዳኝነት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በማንሳት በአደረጃጀቱ የተሰሩ ስራዎች እንደተሞክሮ ሊወሰድ የሚችሉ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በክልላችን የቆየውን ጠቃሚ የባህላዊ ዳኝነትን ተሞክሮ በመጠቀም በዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን እውን ማድረግ እንደሚገባ ክቡር አፌ ጉባኤ አሳስበዋል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም እንደ ሀገር የተጀመረው የፍትህ ሪፎርም ስራዎችን እውን ለማድረግ በክልሉም የፍትህ ተደራሽነት ላይ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል ።

ለተግባራዊነቱ የማህበረሰቡን ፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ በ2016 ዓ/ም በአዋጅ ማቋቋምና በማፅደቅ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ክቡር ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል።

በዚህ መሠረት የማህበራዊ ፍርድ ቤቶች እስከ 20ሺ ብር ድረስ በቀበሌ ደረጃ የዳኝነት አገልግሎት እንዲያገኙ ማሻሻያ መደረጉን አንስተዋል ።

የባህላዊ ፍርድ ቤት በየአካባቢው መደራጀት ዘርፌ ብዙ ፋይዳ መኖሩን በማንሳት ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች የመዝገቦች ጫናን ከመቀነስም በላይ ለዳኞች የስራ ጫናውን በመቀነስ ጥራት ያለ ውሳኔ እንዲሰጡ ድርሻውን ማበርከቱን አቶ ቆጭቶ ገልጸዋል።

በዚህም የማህበራዊና ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በመቋቋሙ በክልሉ አምና ከነበረበት 10ሺ 500 መዝገብ መቀነስ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም ለዚሁ ስኬት ከአዋጅ ዝግጅት፣ አደረጃጀትን ከማጠናከርና ተገቢውን ግንዛቤ በየደረጃው በማስጨበጥ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቀርበዋል።

ጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ደረጀ ሽመልስ ተቋሙ በሀገርቱ ውስጥ በሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ የህግ በላይነትን ከማስፈን፣ የሠላም ዕሴት ግንባታ እና አቅም ከሌላቸው የፍትህ አካላት አቅም በመገንባት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራና ውጤትም እያስመዘገበ ያለ ተቋም እንደሆነ አንስተዋል።

በመሆኑም በተወሰኑ አካባቢዎች የተጀመሩ መልካም ጅምሮችን ወደ ሁሉም አካባቢ በማስፋት ሠላም በማስፈንና ፍትህን ለሁሉም ህብረተሰብ ለማድረስ መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የባህላዊ ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም ሪፖርቱ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እና የምርምር፣ ስልጠና እና ሪፎርም ስራዎች ዳይረክቶሬት ዳይሬክተሩ በአቶ አፋወርቅ ተክሌ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።

በሪፖርቱ በክልሉ ካሉት ቀበሌዎች በ393 የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ስልጠና ተሰጥቶ ከተደራጁት መካከል 196 ወደ ስራ በመግባታቸው 339 ጉዳዮች ከቀረቡት ውስጥ 314 ጉዳዮች ቀርቦ በባህላዊ ዳኝነት እልባት ማግኘታቸው ተነስቷል።

በውይይቱ ጠንካራ ጎኖች እንዲጎለብቱና ክፍተቶችን በጋራ በቅንጅትና በመናበብ አደረጃጀቱን በሁሉም አካባቢ ወጥ ወደ ሆነ አደረጃጀት ለማድረስ መሰራት እንደሚገባ ተነስቷል።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *