


ማሻ ከተማ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ውስጥ ከሚገኙት ከስድስት ዞኖች አንዷ በሆነችው በሸካ ዞን ካሉት ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች አንዷ ናት።
ማሻ በ1903 የተቆረቆረች እድሜ ጠገቧ ከተማ በርካታ የመንግስት አወቃቀሮችን ያሳለፈች ቅርብ ጊዜ የሸካ ዞን የዞኑን መቀመጫ ወደ ቴፒ ከተማ እስኪያዛዉር ድረስ የዞኑ ዋና ከተማ ሆና ሲታገለግል የነበረች ከተማ ነች።
ማሻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዞን ዋና ከተማነት ወጥታ በከተማ አስተዳዳሪነት ራሷን እያስተዳደረች ያለች ለኑሮ ምቹ፣አየሯ ተስማሚ ፣ህዝቡን አቃፊና ሠላሟ የተረጋገጠች በዕድገት ጎዳና ላይ የሚትገኝ ከተማ ናት።
የማሻ ከተማ ከንቲባ አቶ ሠራዊት አየነው ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተማዋ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካ ተሳትፎ ብዙ ተሳትፎ ያላት ጥንታዊት ከተማ እንደሆነች ያነሳሉ።
ለአንድ ከተማ ዕድገት መሠረተ ልማት ወሳኝ ነው ።ማሻ ከተማ የረጅም ጊዜ የመብራት ፣ የውሃ፣ የሆስፒታል ግንባታ ጨምሮ የከተማ ውስጥ የመልማት ጥያቄዎች የነበሩባት አሁን ላይ በለውጡ መንግስት ጥያቄዎቿ ተሰምቶ ምላሽ እያገኘች ያለች ከተማ መሆኑን ይናገራሉ።



በከተማዋ የረዥም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የውሃ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ወደ ግንባታ ሂደት መግባቱ ፣መብራት ጥያቄ ሳቢስተሽን ግንባታ ተጀምሮ እየተጠናቀቀ መሆኑ፣የሆስፒታል ግንባታ ተጀምሮ አፈጻጸሙም የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም ከተማዋ የውስጥ መሠረተ ልማት በUIIDP ፕሮግራም በመታቀፍ የሙከራ ትግበራ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚኝም አቶ ሠራዊት ተናግረዋል።
በከተማዋ የተጀመሩ ስራዎችን በሚመለከት የአፈጻጸም ችግር ካልሆኑ በስተቀር በለውጡ መንግስት ብዙ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እየተመለሱ ናቸውም ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ መሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናቅቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቁ ከመንግስት ለከተማ ልማት የተበጀተው በጀት ስራ ላይ እንዲውል በጀት በመመደብ፣ህዝቡን በማስተባበር፣የአፈጻጸም ሂደቱን በመገምገም ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመንገድ መሰረት ልማትም በሁሉም አቅጣጫ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በፕሮጀክቶቹ ያለዉ የአፈጻጸም አልፎ አልፎም የሚነሳዉ የጥራት ችግር አሁንም የህዝቡ ጥያቄ እንደሆነ ከንቲባዉ ያነሳሉ።
የከተማዋ ህዝብ ለተጀመረው መሠረተ ልማት መጠናቀቅ የጉልበት አስተዋፆኦ እና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ያለው የነቃ ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ ሠራዊት አየነው በቅርቡ ለሆስፒታል ግንባታ ቁሳቁስ ግዥ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
በተለይም በከተማዋ የሆስፒታል ግንባታ፣ የውሃ ፣የከተማ ውስጥ አስፓልት መንገድና የመብራት ጥያቄዎች የህዝቦች የረዥም ጊዜ ጥያቄዎች የነበሩት ከመንግሥት ምላሽ አግኝቶ እየተሰሩ ቢሆንም እነዚህን ከዳር ለማድረስ የክልሉ መንግስት ፣የዞን፣የከተማ አስተዳደር እገዛ እና የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ አሁንም ቢሆን መጠናከር ይገባዋል አቶ ሠራዊት ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማዉ ደረጃቸዉን የጠበቁ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲኖሩ በግሉ ባለሃብት በኩል አሁን እየታየ ያለዉ መነሳሳት የሚበረታታ እንደሆነም ይገልጻሉ።
በቀጣይም በከተማዉ በተለያየ አማራጭ ለማልማት የሚፈልጉ አካላትን የከተማ አስተዳደሩ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አቶ ሠራዊት ጠቅሰዋል።
