የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች መብት፣ደህንነት፣ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተረጋግጧል?

Spread the love

ሪፖርታጂ– አዘጋጅ ዕድገቱ በዛብህ

ከጠቅላላው የአገራችን ህዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሸፍነው ሴቶች ህጻናትና ወጣት የኀብረተሰብ ክፍል ሲሆን ይህም አሃዝ አገራችን ኢትዮጵያ አምራች ሃይል ያላት አገር መሆኗን ያመላክታል፡፡

በመሆኑም ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው ዲሞክራሲ ለማረጋገጥ የሴቶች ህጻናትና የወጣቶች ተሳትፎ ማሳደግና ተጠቃሚነታቸው ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ባለፉት አመታት ብሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ ፤ ብሔራዊ የህጻናት ፖሊሲና ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እንዲሁም የሴቶችና የወጣቶች የእድገት ፓኬጆችን በማዘጋጀትና የአሰራር ስርአት በመዘርጋት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በመሆኑም የሴቶችና ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት ችሏል፡፡ ለአብነት ያህል ባለፉት ዓመታት የገጠር ሴቶችና ወጣቶች በግብርናና ከግብርና ውጭ ባሉ የስራ አማራጮች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ የተቻለ ሲሆን በከተማም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂን በመቅረፅና ተግባራዊ በማድረግ ሴቶችና ወጣቶች በተለያዩ የእድገት ተኮር ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ቁጥራቸው የማይናቅ ሴቶችና ወጣቶችም ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት በመሸጋገር ለሌሎች አርአያ መሆን ችለዋል፡፡

ከክልላችን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ከአጠቃላይ የክልሉ ህዝብ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች አሀዝ ከ90 በመቶ በላይ መሆኑን ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የተገኘው የትንቢያ መረጃ ያሳይል፡፡ ይህንን ታላቅ የልማት ሀይል በዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ባለው የዲሞክራሲ ግንባታ ማሳተፍና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ በክልሉ መንግስት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡

የክልላችን መንግስት የሴቶችና ወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በርካታ ጥረቶችን አድረጓል፡፡ ከነዚህም ዉስጥ መሰረታዊ የሆኑት የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መብቶች ህገ መንግስታዊ መሰረት ማስያዝ ከዚህም ባሻገር በተግባር ማረጋገጥ የሚያስችል ሃገራዊ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎች ፕሮግራሞች ፓኬጆች መሰረት በማድረግ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በማቀድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያተደረገ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ በክልላችን በተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት መላው ህዝቡ፤ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር የተመዘገበው ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ እድገቱ ራሱ የፈጠራቸው አዳዲስ ፍላጎቶች እና አስቀድመው በወጉ ያልተቀረፉ ችግሮች ተደማምረው አሁንም የሴቶች ህጻናትና የወጣቶችን ዘርፈ ብዙና አንገብጋቢ ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ መፍታት አለመቻላቸውን ያሳያል፡፡ ስለሆነም የሴቶች ህጻናትና የወጣቶችን ችግር ግዜ የማይሰጥ፣ ፈጣን እና የተቀናጀ መፍትሄ የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የሴቶችና የወጣቶች ቁጥር፣ የወጣቶች ወቅታዊ ጥያቄ እንዲሁም አገራችን ከደረሰችበትና ልትደርስበት ካቀደችው የእድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣሙ ፕሮግራሞችን በመንደፍ የሴቶችና የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ የአገራችንን እድገት ማረጋገጥ የሚገባ በመሆኑ በትግበራ ላይ የነበሩትን የኢትዮጵያ ሴቶችና ወጣቶች የዕድገት ፓኬጆች በተፈለገው ልክ ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም አካላት ቅንጅታዊ ድጋፍና ርብርብ የሚሻ መሆኑን ነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ የሚገልጹት።

በሕብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን የተዛባ የስርዓተ-ፆታ አመለካከትና ከዚህ የመነጨውን ኢ-ፍትሃዊ የሃብት፣ የስልጣንና የስራ ክፍፍል በማስወገድ የሴቶችን እኩልነት ለማስፈን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኃላፊዋ አሁን ላይ ሴቶች በተደራጀ መልኩ የሚታገሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፈጠር እየተደረገ መሆኑን ገልፀዎል፡፡  በዚህም ከ526 ሺህ 596 በላይ ሴቶች በ18ሺህ 807 በሴቶች ልማት  ህብረት መደራጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሴቶቹ አደረጃጀቶች ነፃነት ያላቸው፣ የዴሞክራሲያዊና ልማታዊ የአስተሳሰብ ልዕልና ባለቤት የሆኑ የበሳል አመራር መፍለቂያ በመሆን በክልሉ የልማት ሠራዊት ግንባታ ውስጥ የጎላ ሚና እንዳለው የሚያነሱት የቢሮው ኃላፊዋ በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ 6ሺህ 700 የሚጠጉ ሴቶችን ለአመራር ብቁ እንድሆኑ ለማድረግና ሴቶችን በተለያዩ አደረጃጀት በማደረጀት የስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትህምህርቶችን መስጠት መቻሉን አብራርተዋል። የሴቶችን ተሳትፎና ውክልና ለማረጋገጥ በቢሮው በተሰራው ስራ በሠላም ግንባታና ግጭት አፈታት ዙሪያ ሴቶች እንዲሳተፉ ማድረግና እንዲሁም የሴቶችን መብትና ሁለንተናዊ ደህንነት ከማስጠበቅ ረገድም ሴቶችን ከተለያዩ ጥቃትና ጎዥ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ሴቶች በገጠር የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ በማድረግ በግብርና ዘርፍ ያላቸው የሀብት ባለቤት ያለመሆንና በወንዶች ላይ የኢኮኖሚ ጥገኝነት ችግር በዘላቂነት የሚፈታበትን ስልት ተቀይሶ በመተግበር ላይ ያለ ሲሆን በዚህም በ2016 ግማሽ ዓመት ብቻ በቁጥር 25ሺህ 598 ሴቶች በክልሉ የገጠር መሬት ማረጋገጫ ሰነድ ማግኘታቸውን የገለጹት ክብርት ወ/ሮ ገነት የገጠር ሴቶች በግብርና ብቻ ሳይሆን ከግብርና ውጭ ባሉ ተያያዥ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ እየሆኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የከተማ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ከተፈጠረው የስራ ዕድል የሴቶች ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን በመንግስት ከተመቻቸው የብድር አገልግሎት ውስጥም የ7 ሺህ 328 ሴቶች 25 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የብድር ተጠቃሚ መሆናቸውን በመጠቆም የሴቶች ቁጠባ መጠንም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ  73.1 ሚሊዮን የደረሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ 12ሺህ 339 የሚጠጉ ሴቶች የህብረት ስራ ማህበራት አባልነት የታቀፉ ስሆን ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከተሰጠው ስልጠናና ከገበያ ትስስር አንፃር የሴቶች ተሳትፎ ድርሻ የጎላ መሆኑን በመጠቆም በክልሉ ሁሉም አከባቢ በተለያየ መልኩ በተፈጠረው የስራ ዕድልም ሴቶች ተጠቃሚ እንደሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

ሴቶች ተልዕኳቸውን በመወጣት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲያበለፅጉ ጤናቸውን መጠበቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሲሆን የጤናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን በተሰጠው ትኩረት በክልሉ የማህፀን መውጣት፣ ጡት ካንስር ፣ፌስቱላ እና የማህፃን ጫፍ ካንሰር ችግር የህክምና አገልግሎት እንድያገኙ ለ139 ሴቶች ህክምና የተመቻቸላቸው መሆኑን አፈያስረዱት የቢሮ ሃላፊዋ ሴቶች በአዳሪ ትምህርት ቤቶችናና በመሠረታዊ የጎልማሶች ትምህርት ተጠቃሚ እንድሆኑ በተሰራው ስራም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በሁሉም የልማት ዘርፎች የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የመንግስት አስፈፃሚ መ/ቤቶች የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ በየእቅዶቻቸው እንዲያካትቱ ብሎም ተቋማዊ በማድረግ በባለቤትነት ይዘው እንዲፈጽሙት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል ሀላፊዋ።

በክልሉ ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች
ዘርፍ እንዲደራጁ በማድረግና የብድር፤ የመስሪያ ቦታ፣ የገበያ ትስስርና የስልጠና ሁለገብ ድጋፍ በመስጠት ከልማቱ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት እንዲላቀቁ በተሰራው ተግባር ውጤት የተመዘገ ሲሆን በአጠቃላይ የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በተሰጠው ትኩረት ከ40 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች በመደራጀት ከዚህም ውስጥ ከ20 ሺህ 500 የሚልቁ ቁጠባ በማስቀመጥ የብድር አግልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች በ2016 በጀት አመት በ6 ወር ወደ 20 የሚጠጉ የወጣቶች የስብእና ግንባታ ማእከላትን መልሶ በማደራጀት ከ26 ሺህ 484 በላይ ወጣቶች የቤተ-መጻህፍት፣ የመረጃ ቴክኖሎጅ፣ የመዝናኛ፣ የስነ ተዋልዶ ጤና፣ የኤች ኣይ ቪ የምክር፣ የስልጠና እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ወጣቶች በሀገሪቱ ውስጥ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የልማት እንቅስቃሴ፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍና በሂደቱም ከማህብረሰቡ መልካም ልምዶች በመቅሰም የስራ ባህላችውን ለማዳበር በተለያዩ የሲቭል ማህበረሰብ አደረጃጀት በመታቀፍ እምቅ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም እንዲሁም ለማህበረሰቡ ጠቃሚ በሆኑ  መስኮች በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በመስጠት የራሳቸውንና የሌላውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን፤ በ2015 ክረምት በጎ ፈቃድ በ13 መስኮች 601,303 በጎ ፋቃደኞች በማሳተፍ 1,162,800 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ 430,236,000 ብር የሚገመት በመንግስት የሚወጣውን ወጪ ለማዳን ታቅዶ በዚህም 605, 952 ወጣቶችን በማሳተፍ 2,031,473 ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ በማድረግ ብር 515,138,362 ከመንግስት ይወጣ የነበረ ወጪ ማዳን ተችሏል ብለዋል ክብርት ወ/ሮ ገነት፡፡

የህጻናት መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በተሰራው ስራ ያለእድሜ ጋብቻ ምጣኔ በመቀነስ የማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በርካታ ማህበረስብ አቀፍ ተግባራትን በማከናወን ውጤቶች በመመዝገብ ላይ እንዳለ የተገለፀ ስሆን የህጻናት ተሳትፎ ለማሳደግ በተለያዩ አደረጃጀት በማሳተፍ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ነው የቢሮ ሀላፊዋ ያስረዱት ።

በመጨረሻም የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ አሁንም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቅንጀት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ክብርት ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በአፅኖዖት ያሳሰቡት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *