አርሶና አርብቶ አደሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት እንዲቀየርና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሻሻል በልዩ ትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ፦አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

የገጠር መሬት ባለይዞታዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ላይ ትኩረት ያደረገ የንቅናቄ መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

መድረኩ ”ዲጂታል ማንነት ለተረጋገጠ የይዞታ ባለቤትነትና ለላቀ የፋይናንስ ተጠቃሚነት’ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን ይህም የክልሉ ግብርና ቢሮ ከኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴር በጋራ ትብብር ያዘጋጀው ነዉ።

በመድረኩ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለጹት፣ የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆን የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት እንዲቀየር እና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሻሻል ምቹ ነባራዊ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው።

በክልሉ ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንዲያገኙ ታቅዶ እየተሰራ እንዳለና እስካሁን ከ600 ሺህ ያልበለጡ ዜጎች ብቻ መመዝገባቸውን አስረተዉ ዕቅዱን ለማሳካት በቀሪ ወራት የተጠናከረ ንቅናቄ በማድረግ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በገጠር ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ ነው ያሉት አቶ ፍቅሬ አማን፤ የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ድጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት በማሻሻል ከባህላዊ የእርሻ ሥርዓት ወደ ዘመናዊ እንዲሸጋገሩ የተጀመረው ሥራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላልም ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አካላት ንቅናቄውን በባለቤትነት በመምራት ሂደቱን በየጊዜው እየገመገሙ መሄድ ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ፍቅሬ አማን፤ ለሥራው ማነቆ የሚሆኑ ጉዳዮች በየደረጃው እንዲፈቱ ትኩረት ይደረጋልም ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸዉ በወቅቱ እንዳሉት፤ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫን ከዲጂታል ስርዓት ጋር ማገናኘት የብድር እና ሌሎች የፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማሻሻል ይረዳል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለገጠር ትራንስፎርሜሽን መሳካት ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ማስረሻ በላቸው፤ ለንቅናቄው ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ ተቋማትና አካላት ሚናቸውን በተገቢው እንዲወጡ አሳስበዋል።

የንቅናቄው መድረክ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ክልላዊ የዲጂታል መታወቂያ ንቅናቄ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው ተግባራትን ቆጥረው በመረከብ ሚናቸውን በተገቢው እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *