ሁለንተናዊ ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አመራር ቁርጠኝነት መጠናከር አለበት – አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት ክልላዊ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ እየገመገመ ይገኛል።

በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፥የዜጎችን ሁለንተናዊ ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ቁርጠኝነት መጠናከር አለበት ብለዋል።

ባለፉት ጊዜ በቅንጅት በተሰራው ውጤታማ ሥራ የክልሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና አፈጻጸም እንደ ሀገር የተሻለ እንደነበረ የገለጹት አቶ ፍቅሬ፥ ይሁን እንጂ ውጤቱን በዘላቂነት ከማስቀጠል አኳያ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

በክልሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አፈጻጸም ሰፊ ልዩነት ያለው ነው ያሉት አቶ ፍቅሬ፥ ለአፈጻጸሙ ማነስ ማነቆ የኾኑ ጉዳዮችን በመድረኩ በመገምገም አመራሩ ተግባሩን በትኩረት መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የማህበራዊ ልማት ሥራዎቻችን ከብልፅግና ፓርቲ ሰው ተኮር ዕሳቤ የተቀዱ ናቸው ያሉ አቶ ፍቅሬ፥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች ተደራሽነትና አካታችነት ባለው መልኩ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና ተግባርን በቁርጠኝነት ማሳካት ይገባል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በዘርፉ የሚስተዋለውን የአግልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን በመፍታት የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ መጠነ-ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት አቶ ፍቅሬ የመድኃኒት አቅርቦት መሻሻሉን ጠቁመዋል።

በመድረኩ በየዞኑ ያለው የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርበው በዝርዝር በመገምገም በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ የአዲስ አባል ማፍራትና የነባር ዕድሳት ለማጠናቀቅ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት እንደኾነም ተገልጿል።

በአፈጻጸም ግምገማ መድረኩ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *