በክልሉ በካፒታል በጀት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በተገቢው ተጠናቅቆ የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል:-የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ

Spread the love

የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች ባደረጉት የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ምልከታ ዙሪያ የግብረ መልስ መድረክ በታርጫ ከተማ ተደርጓል።

የክልሉ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በክልል በሁሉም አከባቢዎች በካፕታል በጀት እየተሰሩ ያሉ ወደ 20 የሚጠጉ የጤና፣ የውሃ እንዲሁም የኮሌጆች የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

የአስፈፃሚ ተቋማት በፅሁፍ የሚያቀርቡትን ሪፖርት በተግባር በማረጋገጥ ለፕሮጀክቶች አፈፃፀም ትኩረት እንዲሰጥ ማስቻል የመስክ ምልከታ ዓላማ እንደሆነ የመስክ ምልከታ ቡድን አስተባባሪ አቶ አዲስምዕራፍ አለሙ አብራርተዋል።

በፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት የተስተዋሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

ለፕሮጀክቶቹ መዘገየት የካፕታል በጀት ውስንነት፣ የግንባታ እቃዎች ዋጋ ወጥ ያለመሆን፣ የታችኞቹ መዋቅሮች የማችንግ ፈንድ አለመያዝ፣ በኮንትራክተሮች የሚቀርብ ተደጋጋሚ የዋጋ ማሻሻያ ጥያቄ፣ የዲዛይንና የሳይት መረጣ ክፍተቶች በዋናነት ተነስቷል።

የግብረ መልስ መድረኩን የመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በክልሉ በካፕታል በጀት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በተገቢው ተጠናቅቆ የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዋና አፌ ጉባኤው ፕሮጀክቶችን በተገቢው ማጠናቀቅ በህዝብ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

አቶ ወንድሙ አክለውም ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ የተጀመሩትንና በቀድሞ የደቡብ ክልል የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የሚደረጉ ጥረቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ እንደሆነም አንስተዋል

የተለዩ ክፍተቶችን በመፍታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚመለከተው የባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራ በግብረ መልሱ የተሳተፉ የቢሮ ሀላፊዎች ተናግረዋል።

የኮንስትራክሽን ባለስልጣን በክልሉ ያሉ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ሰብሰብ በማድረግና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተገቢው በመገምገም በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ሰጥቶ ልሰራ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በክልሉ ምክር ቤት የተጀመሩ የፕሮጀክት አፈፃፀምና የአገለግሎቶች አሰጣጥ የድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ዋናና ምክትል አፌ ጉባኤዎች፣ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና የተለያዩ ቢሮዎች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *