


የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራር በመቅረፍ እንግልትን ከመቀነስ ባለፈ ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ በመንግሥት የተነደፈ የሪፎርም አሰራር መሆኑን የደቡብ ምዕራብ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሥራት አዳሮ ገለጹ።
በሚዛን ብዝሃ ማዕከል አማን ከተማ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የደቡብ ምዕራብ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ከጀመረ በአንድ ወር ውስጥ ከ2ሺህ 7መቶ በላይ ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠት መቻሉን የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሥራት አዳሮ ገልጸዋል።
ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የክልሉ መሶብ አገልግሎት በዘጠኝ ክልልና ፌደራል ተቋማት 28 የተለያዩ አገልግሎቶች መስጠት መጀመሩንና አገልግሎቱ አሁን ላይ ሰፍቶ ወደ 35 ማደጉንም ተናግረዋል።
ማዕከሉ የህዝብ እሮሮ ፥ለሙስና የተጋለጡ፥ እንግልት እና የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ የሆኑ አገልግሎቶችን ማለትም በዲጂታል አገልግሎት ከእጅ ንክኪ በጸዳ መልኩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የኦን- ላይን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያነሱት።
አሁን ላይ በክልሉ በመሶብ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ከዘጠኝ ፌደራልና ክልል ተቋማት በተጨማሪ ሌሎች በብዛት የህዝብ አገልግሎት የሚያገኙባቸው ፣ የመልካም አስተዳደር አስተዳደር ጥያቄ የሚነሳባቸዉ የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የክልል ተቋማት ተለይተው ሶፍትዌር ለምተው የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሰጡ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከክልል ማዕከል በተጨማሪም በዞን የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ማስፋት እና ማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው አቶ አሥራት አዳሮ የተናገሩት።
በአምስት ዞኖች የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር የሚያስችል የቅድሜ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ይኽም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ በከንቲባ የሚመሩ ከተሞች የመሶብ አንድ ማዕከል መስጫ በመገንባት የህዝቡ አንገብጋቢ አገልግሎቶች ተለይተው አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከሚመለከታቸው ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያብራሩት።
የመንግስት እና ፓርቲ አዲስ ኢንሼቲቭ የኾነው የመሶብ አገልግሎት ህዝቡን በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ያለምንም እንግልት የሚያስገኝ አዲስ ሪፎርም አሰራር በመሆኑ ህዝቡም በሚፈልጉበት ጊዜ መተው እንዲገለገልም ጥሪ አቅርበዋል።
በፍቅር ከበደ
