




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በታርጫ ከተማ አስተዳደር 02 ቀበሌ አረንጓዴ መንደር ለአቅመ-ደካማ ሴት ያስገነባውን ቤት መርቀው አስረክበዋል።
በርክብክቡ ወቅት የተገኙት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጥላሁን ታደመ የመንግስት ተቋማት ከመደበኛ ስራቸዉ ጎን ለጎን በሰብዓዊ እና ማህበራዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት ሰጥተዉ እንዲሰሩ ጥሪ አቀርበዋል።
አክለውም የመንግስት ተቋማት ከመደበኛ ስራቸዉ ጎን ለጎን በማህበራዊ አግልግሎት ስራዎች ላይ መሳተፋቸው ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ከፈጣሪ ዘንድም ዋጋ ያለዉ ቅዱስ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።
ለቤቱ ግንባታ አጠቃላይ የወጣ ወጪ ከ320,000/ሶስት መቶ ሀያ ሺህ ብር/ በላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተሸፈነ መሆኑን የገለፁት ምክትል ፕረዚዳንቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በዚህ በጎ ተግባር ሲሳተፍ ከዚህ በፊት በክልሉ ሸካ እና ኮንታ ዞኖች የተሰሩትን ጨምሮ ይህ ለ3ኛ ጊዜ መሆኑን ገልፀዋል።
ቤቱን ገንብቶ ከመስጠት በተጨማሪ ለአቅመ_ደካማዋ ሴት ቀጣይ ማቋቋሚያና ስራ ማስጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ ለከተማ አስተዳደሩና ለከተማው ሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ያስረከቡት ምክትል ፕረዚዳንቱ አቅመ_ደካማዋ ሴት ቀጣይ ስራ በሚትጀምርበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ልሰጥበት እንደምገባም አሳስበዋል።
ለቤቱ ግንባታ ሂደት በሀሳብ፣ በገንዘብና በክትትል የተሳተፉትን አካላት በተለይም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታርጫ ምድብ ችሎት ዳኞች፣ የዳዉሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የታርጫ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችን እና የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያን አመስግነዋል።
የዳዉሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕረዚዳንት የሆኑት አቶ አሮታ አልባዞ በበኩላቸዉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቦታ ርቀት ሳይገደብ የስራዉን ፍጥነትና ጥራት በመከታተል በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ቤቱን ማስመረቁ እጅግ የሚደነቅ እና ለሌሎች አርአያ የሚሆን ስራ ነዉ ብለዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የታርጫ ከተማ አስተዳደር ካንቲባ አቶ አስናቀ አበበ የለዉጡ መንግስት ያስቀመጠውን ሰዉ ተኮር ፖሊሲ በመከተል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከመደበኛ የዳኝነት ስራዉ ጎን ለጎን በማህበራዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ተቋሙ የህዝብ አገልጋይ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ ምስጋና አቀርበዋል።
ቤቱ በተሻለ ጥራትና በዉሉ ከተቀመጠዉ ጊዜ ሳያልፉ ተሰርቶ መረከቡ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ስራ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም አቅመ_ደካማ ሴትን ስራ ለማስጀመር ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቀረበው ገንዘብ ላይ ከከተማ አስተዳደሩ 20,000 ብር በመጨመር በተሻለ ሁኔታ ስራ እንደሚያስጀምሩ ገልፀዉ በሂደቱ ላይ የተሳተፉትን አካላት ሁሉ አመስግነዋል።
የቤቱ ባለቤት ወ/ሮ ሳራ ባቴም ባጋጠማቸዉ ችግር ምክኒያት ተስፋ ከቆረጥኩበት ወጥቸያለዉ በማለት በተደረገላቸው ድጋፍ እጅግ በጣም ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸዉ መሆኑን ገልፀዋል።
በርክብክቡ መርሃ ግብሩየተገኙ የዳውሮ ዞን ሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሪት ፀጋነሽ ሽታዬ እና የታርጫ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ገትነት ምስጋና አቀርበዋል። መረጃው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነዉ።
በጌታሁን ግርማ
