አመራሩ የልማት አቅሞችን በመጠቀምና ከህብረተሰቡ ጋር ተግባቦት በመፍጠር በቀጣይ አጭር ጊዜያት ውስጥ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶች ለማስመዝገብ መስራት ይገባል፤ አቶ ታከለ ተስፉ

Spread the love

በኮንታ ዞን ላለፉት 9 ቀናት “በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ቃል ለ3ኛ ዙር የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና እየተጠቃለለ ይገኛል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ እንደ ሀገር የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በአመራሩ ዘንድ የአመለካከትና የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር ተቀዳሚ ተግባር ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ከዚህ መነሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሎም በክልል ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን ማስፋፋት በሚቻልበት ሂደት ላይ ስልጠና መሰጠቱን አንስተው በተለይም የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን እመርታ፣ የኢንዱስትሪ መንደር እመርታ፣ የከተማ ልማት እመርታ እና የቱሪዝም ዘርፍ እመርታ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በማተኮር የተሰጠ ስልጠና እንደሆነ አስረድተዋል።

አመራሩ የልማት አቅሞችን በመጠቀምና ከህብረተሰቡ ጋር ተግባቦት በመፍጠር በቀጣይ አጭር ጊዜያት ውስጥ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ባለፉት 9 ቀናት ቆይታ ከነበረው ስልጠና መነሻ በዞኑ እንደጉድለት በተነሱ ጉዳዮች ላይ መንግስት በዕቅድ እየሰራባቸው እንደሚገኝ ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው በግብርና ስራ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻል፣ የኢኮ ቱሪዝም ዘርፍ ማጠናከር፣ ኢንዱስትሪን ከግብርና ጋር ማስተሳሰር፣ የከተሞችን መሠረተ ልማት ማስፋፋትና ጽዱ ማድረግ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው አስገንዝበዋል።

አቶ ታከለ አክለውም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ሊፈፀሙ ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የዞን ስራ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ የዞኑ ፑል አመራሮች፣ የወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ስራ አስፈፃሚዎች፣ የሁሉም መዋቅሮች አመራር አካላት ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *